Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የዓድዋ ድል አፍሪካ እጣ ፋንታዋን በራሷ መበየን እንደምትችል ያረጋገጠ ነው – ሙሳ ፋቂ ማህማት

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓድዋ ድል አፍሪካ እጣ ፋንታዋን ያለማንም ጣልቃ ገብነት በራሷ መበየን እንደምትችል ያረጋገጠ ነው ሲሉ የቀድሞው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ገለጹ።

129ኛው የዓድዋ ድል በዓል “ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል” በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።

የቀድሞው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት በበዓሉ አከባበር ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የዓድዋ ድል ጦርነትን የማሸነፍ ታሪክ ብቻ አደለም ብለዋል።

የዓድዋ ድል ለመላ ጥቁር ህዝቦች የይቻላል አስተሳሰብን ያሰረፀ እንዲሁም በአንድነትና ትብብር የአፍሪካን መፃኢ ዕድል የተሻለ ማድረግ እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

አፍሪካ ለደረሰባት በደል ካሳ የምትጠይቅበት ዓመት እንደመሆኑ በዓሉ ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥራል ነው ያሉት።

አፍሪካዊያን ከተባበሩና በአንድነት ከቆሙ የማይሳኩ የሚመስሉ ድሎችን ማስመዝገብና የተሻለ አህጉር ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚችሉም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የነፃነት ቀንዲልና የአፍሪካዊያን ተምሳሌት መሆኗንም በቅርቡ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች እየታዩ ያሉ የልማት ስራዎች ምስክር ናቸው ብለዋል።

ድሉ አፍሪካ የራሷን እጣ ፋንታ ያለማንም የውጭ ሃይል ጣልቃ ገብነት መበየንና መቅረፅ እንደምትችል ያረጋገጠ መሆኑንም በአፅንኦት መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version