አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው ለዩክሬን የምታደርገው ወታደራዊ ድጋፍ በጊዜያዊነት እንዲቋረጥ መወሰናቸው ተገልጿል።
ውሳኔው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከዩክሬን አቻቸው ቮሎድሚር ዘለንስኪ ጋር ከቀናት በፊት በነጩ ቤተመንግስት ያደረጉት ውይይት ባለመግባባት መቋጨቱን ተከትሎ የተደረሰ ነው።
አሜሪካ ውሳኔውን ያሳለፈችው ለዩክሬን የምታደርገው ድጋፍ መፍትሄ ማምጣት በሚያስችል አግባብ ጥቅም ላይ መዋሉን ለመገምገም እንደሆነ ተጠቅሷል።
በአሜሪካ ውሳኔ ዙሪያ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪን ብጠይቅ ምላሽ አጣሁ ያለው የሬውተርስ የማለዳ ዘገባ በዋሽንግተን የዩክሬን ኤምባሲም ዝምታን መምረጡን አስነብቧል።
አሜሪካ ባለፉት ሶስት ዓመታት ለዩክሬን የ175 ቢሊየን ዶላር አጠቃላይ ድጋፍ ማደርጓ ይታወሳል።