አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ላይ በፍጻሜው ዕለት አዳዲስ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡ የፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ተናግረዋል።
በዚህ መሰረትም በፍጻሜው ጨዋታ በእረፍት ሰዓት በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሙዚቃ ዝግጅት እንደሚቀርብ ነው የገለጹት፡፡
የዓለም ዋንጫ ከጀመረበት ከፈረንጆቹ 1930 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው ዝግጅት ላይ የሙዚቃ ሥራቸውን የሚያቀርቡ አርቲስቶችን የመምረጥ ሒደት መጀመሩን አመልክተዋል፡፡
በአሜሪካው ታዋቂ ሱፐር ቦውል ፍጻሜ ጨዋታ ላይ የሚቀርበው የሙዚቃ ዝግጅት ተወዳጅነትን ማትረፉ ፊፋ መርሐ ግብሩን እንዲያዘጋጅ መነሻ እንደሆነው ቢን ስፖርት ዘግቧል፡፡
የ2026ቱን ዓለም ዋንጫ አሜሪካ፣ ሜክሲኮና ካናዳ በጥምረት የሚያዘጋጁት ሲሆን÷ የፍጻሜ ጨዋታው በአሜሪካ ኒው ጄርሲ ግዙፉ ሚትላይፍ ስታዲየም ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።