አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግስት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ያለውን ጽኑ አቋም በተግባር ማሳየቱን የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ገለጹ።
ሚኒስትሩ መንግሥት ከለውጡ በፊት የነበሩ የፖለቲካ ስብራቶችን ለመጠገን፣ የትኛውም ፖለቲካዊ ችግር በውይይት መፈታት እንዳለበት ግልፅ አቋም በመያዝ በርካታ ርምጃዎችን መውሰዱን አስረድተዋል።
በዚህም ኢትዮጵያን ለውስብስብ ችግር የዳረጉ ኋላ ቀር የፖለቲካ ልምምዶችን እና ነጠላ ትርክቶችን የማረቅ ስራን በስፋት ማከናወኑን ነው የተናገሩት።
የፖለቲካ ዓላማቸውን በኃይል ለማሳካት ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ፍላጎታቸውን ወደ ጠረጴዛ ውይይት እንዲያመጡ ሁልጊዜ ለሰላም በሩን ክፍት በማድረግ ብዙ ርቀት መጓዙን አንስተዋል።
በዚህም በርካታ የታጠቁ አካላት ከኃይል አማራጭና ከግጭት ጉዳት እንጂ ጥቅም እንደሌለ በመገንዘብ የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለሰላምና ለልማት የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
መንግስት ዘላቂ ሰላም በማስፈን እና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር የሀገረ መንግሥት ግንባታን እውን ለማድረግ አሰባሳቢ ትርክቶችን የማጠናከር ሥራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡
መንግስት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ያለውን ጽኑ አቋም በተከታታይ በተግባር ማሳየቱን ገልጸው÷ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በመሆኑም የፖለቲካ ልሂቃን ሰላምን የሚያጸኑ እና አንድነትን የሚያጠናክሩ ሀሳቦችን በማፍለቅ ሚናቸውን እንዲወጡ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የበለጸገች ሀገርን ለመገንባት የሁሉም ዜጋ ተሳትፎና ርብርብ እንደሚያስፈልግም ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡ በሌላ በኩል ሰላም ሚኒስቴር በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶችን በማሰልጠን ብሔራዊ መግባባት የሚፈጥሩ እና አብሮነትን የሚያጠናክሩ ባህሎች እንዲጎለብቱ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በዚህም በ12 ዙሮች ከ70 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማሰልጠን የሕዝቦችን ተጠቃሚነትና አንድነት የሚያጎለብቱ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል፡፡