አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኩባንያው በዘመናዊ መንገድ እንጆሪ እና ለመድኃኒት ግብዓት የሚውል ሳፍሮን የተሰኘ አበባ በማምረት ለውጪ ገበያ ማቅረብ የሚያስችለውን ሥራ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ለመጀመር ስምምነት ፈረመ፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱን የፈረሙት፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሰሐ ይታገሱ (ዶ/ር) እና የአፍሪካን ፋርሚንግ ኢንዱስትሪስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናሱር ማሃማት ናቸው፡፡
ናሱር ማሃማት በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኩባንያው ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ በቨርቲካል ፋርሚንግ በማምረት ወደ ውጭ ይልካል፤ በዚህም ኢትዮጵያን ግንባር ቀደም የእንጆሪ እና ሳፍሮን ላኪ ሀገር ለማድረግ ይሠራል፡፡
ለዚህም ኩባንያው በቻድ ያካበተውን ልምድ ተጠቅሞ በኢትዮጵያ የተሻለ ሥራ እንደሚሠራ ማረጋገጣቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡
ፍሰሐ ይታገሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኩባንያው ይዞት የመጣው ፕሮፖዛል በኮርፖሬሽኑ የሥራ ሂደት ውስጥ አዲስ መሆኑን በመጥቀስ ለውጤታማነቱ ተገቢው ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡
በስምምነቱ መሠረት ኩባንያው በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ 5 ሺህ ካሬ ሜትር የለማ መሬት እና 3 ሺህ ካሬ ሜትር ሼድ ተረክቦ ወደ ሥራ የሚገባ ይሆናል፡፡
በ2 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ኢንቨስትመንት ወደ ሥራ የሚገባው ይህ ኩባንያ፤ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድልን እና ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚም የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚፈጥር ይጠበቃል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል ኩባንያው ሥራ ሲጀምር አፈር ሳይጠቀሙ ምርት ማምረት የሚያስችል ዘመናዊ አሠራር ለኢትዮጵያ ያስተዋውቃል ነው የተባለው፡፡