Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ከ9 ቢሊየን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ባለፉት ስድስት ወራት ከታክስ በፊት 9 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሀብታሙ ኃይለ ሚካኤልን ጨምሮ የተቋሙ ሥራ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ምልከታ እያደረጉ ይገኛል።

በዚሁ ወቅት በተቋሙ የቢዝነስና ዴቨሎፕመንት መምሪያ ኃላፊ ብርሃኔ ገብረእግዚአብሔር የስድስት ወራት አፈፃፀም ያቀረቡ ሲሆን÷ ተቋሙ የሀገሪቱን የገቢና ወጪ ንግድ በማሳለጥ ረገድ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።

ከዕለት ፍጆታ ዕቃዎችና ሸቀጦች ጀምሮ ልዩ ልዩ የፋብሪካ ውጤቶችን፣ አነስተኛና ትላልቅ ማሽነሪዎችን፣ ተሸከርካሪዎችን፣ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን እና የተለያዩ ጭነቶችን በባህርና በየብስ ትራንስፖርት በማጓጓዝ የተሟላ የሎጅስቲክስ አገልግሎት እየሰጠ እንዳለም ተናግረዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት 3 ነጥብ 9 ሚሊየን ቶን የገቢና የወጪ ንግድ ጭነት አገልግሎት መስጠቱን ጠቅሰዋል።

ከሚሰጣቸው አገልግሎቶችም በግማሽ ዓመቱ 44 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ ከ46 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገልፀዋል።

ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ99 በመቶ ብልጫ እንዳለው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በዚህም ተቋሙ ከታክስ በፊት 6 ቢሊየን ብር ለማትረፍ አቅዶ 9 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ትርፍ ማግኘቱንና ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ188 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ነው የገለጹት።

Exit mobile version