የሀገር ውስጥ ዜና

በክልሉ በ5 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ወጪ ለሚገነቡ ሕንጻዎች ስምምነት ተፈረመ

By Adimasu Aragawu

March 13, 2025

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በብዝሃ ዋና ከተሞች ለቢሮ ሥራ አገልግሎት የሚውሉ ሕንጻዎች ግንባታ ለማከናወን ከሦስት የተለያዩ የግንባታ ሥራ ተቋራጮች ጋር የውል ስምምነት ተፈራርሟል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት÷ለሚገነቡት ሕንጻዎች የዲዛይን ዝግጅትና አስፈላጊ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቁመው፤ የጨረታ ሒደቱም ከቅሬታ ነጻ በሆነ መንገድ መከናወኑን አስረድተዋል።

የቢሮ ሕንጻዎቹ ግንባታ 5 ነጥብ 763 ቢሊየን ብር ወጪ እንደሚጠይቅ ነው የገለጹት፡፡

ግንባታው በ2 ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመው÷ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ጥራታቸውና ደረጃቸው ተጠብቆ እንዲከናወኑ አማካሪዎችና ተቋራጮች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ተቋራጮቹ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ወደ ሥራ እንዲገቡ እንደሚደረግና የዝግጅት ሥራዎች በትኩረት እንደሚከናወኑ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

የግንባታ ሒደቱንና የማማከር አገልግሎቱን የክልሉ ግንባታ ዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን ከኦሮሚያ ኢንጀነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር በቅንጅት እንደሚመራ የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።