ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ጋር ተወያዩ

By Hailemaryam Tegegn

March 13, 2025

ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ ክልል አቀፍ ምክክሩን በስኬት ለማከናወን በሚያስችሉ ሂደቶች ላይ መምከራቸው ተገልጿል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ውይይቱን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ÷ በክልሉ በሚካሄደው የምክክር ሂደት ውስጥ መላው ሕዝብ ንቁ ተሳታፊ መሆን እንዳለበት መነሳቱን ተናግረዋል።

በክልሉ ያለውን ግጭት ለማስቆምና የተሻለውን ሰላም ለመትከል ሁሉም ለምክክር ልቡን መክፈት እንዳለበት ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ሕዝቡ የግጭት ምክንያቶችን ከመሰረቱ በመለየት በሀገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ይዞ መቅረብ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በግጭት ውስጥ ያሉ ታጣቂዎችም ችግሮችን በንግግር ለመፍታት ጥያቄዎቻቸውንና አጀንዳቸውን በሚመቻቸው መንገድ ለኮሚሽኑ እንዲያቀርቡም ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ጠይቀዋል።

ሚዲያዎችም የኮሚሽኑን ቁርጠኛ የሰላም አቋም በማሳወቅና ሕዝብን ለሰላም በመቀስቀስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል።

በአማራ ክልል አካባቢዎች ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ እና ደብረ ብርሃን ብሎ በመመደብ የአጀንዳ መነሻ ሐሳቦችን የማሠባሠብ ሥራ በስኬት መከናወኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ÷ በክልል ደረጃ የሚሳተፉ ወኪሎችንም መምረጥ ተችሏል ብለዋል።

የአማራ ክልል መሪዎች እና ሕዝቡ ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ እንደሆነም አመላክተዋል።

አሁን ላይ እንደሀገር በሚደረገው ዋናው ምክክር የሚቀርቡ የአማራ ክልል አጀንዳዎችን በማሰባሰብ ላይ ነን ያሉት ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)÷ በመጨረሻው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ ክልሉን ወክለው የሚሳተፉ ተወካዮችም እየተመረጡ መሆኑን ተናግረዋል።