አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የዋን ዋሽ ፕሮግራም ከ344 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባ የአዩን የባለብዙ መንደር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በሶማሌ ክልል ኖጎብ ዞን፣ በአዩን ወረዳ ተጀመረ፡፡
በወቅቱ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ እንደተናገሩት÷ ከለውጡ ወዲህ በክልሉ በውሃ፣ በጤና እና በትምህርት የልማት መስኮች ውጤት ተመዝግቧል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) በበኩላቸው÷ የውሃ ሽፋን ከክልል ክልል፣ ከአካባቢ አካባቢ ወጥነት እንደሌለው አንስተው፣ በተለይ ውሃ አጠርና ድርቅ የሚያጠቃቸው አካባቢዎችን ታሳቢ በማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በ21 ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን 37 ሺሕ የአካባቢ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡