Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

ምክር ቤቱ በቅድሚያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራርና የማኅበረሰብ አቀፍ ድጋፍና እንክብካቤ ጥምረት ምክር ቤትን ለማቋቋም፣ አደረጃጀቱንና የሃብት አሰባሰብ ሥርዓትን ለመወሰን በወጣው ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቷል።

ማኅበረሰቡን መሠረት ያደረገ የድጋፍና እንክብካቤ ሥርዓትን በመዘርጋት ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስጋቶች ምላሽ ለመስጠት፣ ሃብት የማሰባሰብ አቅምን ለማጎልበት፣ የተረጂነት ስሜትን ለማስወገድ፣ የህዝቡን የመረዳዳት ባህልን ለማጠንከር የሚረዳ መሆኑ ተመላክቷል።

በተለይ የክልሉን ማኅበረሰብ፣ ሲቪክ ማኅበራትን፣ የንግድ ዘርፉን እንዲሁም በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበርና በማሳተፍ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር የተጋለጡ ዜጎችን በዘላቂነት መርዳትና ማቋቋም የሚያስችል የማኅበረሰብ አቀፍ ድጋፍና እንክብካቤ ጥምረትን ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ደንቡ መዘጋጀቱ ተገልጿል።

በዚህም መስተዳድር ምክር ቤቱ በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ በማፅደቅ ስራ ላይ እንዲውሉ ውሳኔ አሳልፏል።

እንዲሁም በሌሎች አጀንዳዎች ዙሪያ ምክር ቤቱ ውሳኔ ማስተላለፉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version