የሀገር ውስጥ ዜና

በቀጣይ 10 ቀናት ለዝናብ መፈጠር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ገጽታዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

By Hailemaryam Tegegn

March 21, 2025

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሚቀጥሉት 10 ቀናት በአብዛኛዎቹ የበልግ አብቃይ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለተዘሩ ሰብሎች እድገት አመቺ የአየር ሁኔታ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡

በቀጣይ ቀናት የሚጠበቀው ርጥበት የአፈር ውስጥ ርጥበትን ስለሚያሻሽል ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት በጎ ጎን እንደሚኖረውም የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

ለዝናብ መፈጠር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የአየር ሁኔታዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ሲሆን÷የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች በርካታ ቦታዎችን የሚሸፍን ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል የመካከለኛው፣ የሰሜን ምስራቅና የደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች በ24 ሠዓት ውስጥ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ነው የተገለጸው፡፡

በተለይም በጋምቤላ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና በምዕራብ አማራ አካባቢዎች ላይ የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት ከ35 እንዲሁም በጥቂት ስፍራዎቻቸው ላይ ከ40 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንደሚሆን የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ።

በአንጻሩ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የጎርፍ መፍሰሻዎችን በማጽዳት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል፡፡