የሀገር ውስጥ ዜና

የምስራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል የቀጣናውን ሀገራት ትስስር ያጠናክራል – ሚኒስትሮች

By Melaku Gedif

March 21, 2025

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል የቀጣናውን ሀገራት ትስስር ለማጠናከር የላቀ ሚና እንዳለው የአፍሪካ ሀገራት ባህልና ስፖርት ሚኒስትሮች ገለጹ።

2ኛው የምስራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል “ጥበብና ባህል ለቀጣናዊ ትብብር” በሚል መሪ ሐሳብ በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

የሩዋንዳ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ናዲያ አሮኝ፥ ፌስቲቫሉ አፍሪካውያን ባህላዊና ጥበባዊ እሴቶቻቸውን በጋራ የሚያሳዩበት መድረክ ነው ብለዋል።

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ኢንገንዚ ኢንዶኒ በበኩላቸው÷የአፍሪካውያን የቋንቋ፣ የባህልና የአኗኗር እሴት ተቀራራቢ በመሆኑ ፌስቲቫሉ ጥምረታቸውን በጋራ የሚያሳዩበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የባህል ፌስቲቫል በሀገራቱ ህዝቦች መካከል የእርስ በርሰ ትውውቅን ለማጠናከር ትልቅ ሚና እንደሚጫወት የገለጹት ደግሞ የቡሩንዲ የምስራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ጉዳዮች የወጣቶች ስፖርትና ባህል ሚኒስትር ጌራቪስ አባየሆ ናቸው፡፡

ሀገራቱ ቀጣናውን በልማት ከማስተሳሰር ባለፈ የባህል ትውውቅ በመፍጠር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ መግለጻቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡