አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ከአልጄሪያ የኢነርጂ፣ ማዕድንና ታዳሽ ኃይል ሚኒስትር መሐመድ አርካብ ጋር ተወያይተዋል።
ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መረጃ÷ በሁለቱ ሀገራት የንግድና የኢነርጂ አስተዳደር ትብብር ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርገናል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያና አልጄሪያ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተው፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ለማስፋት በቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ከአልጄሪያ ጋርም የንግድ ትስስራችንን ለማጠናከር በምንችልባቸው አግባቦች ዙሪያ ገንቢ ውይይት አድርገናልም ነው ያሉት፡፡
አልጄሪያ በኢነርጂ ልማትና አስተዳደር የዳበረ ልምድ እንዳላት ገልጸው÷ በዚህ ረገድ ለምንሰራቸው ስራዎች አጋዥ የሚሆኑ የቴክኒክና የስልጠና ልውውጦችን ለማድረግ ተስማምተናል ብለዋል፡፡
ልዑካን ቡድኑ ኢትዮጵያ ባካሄደችው ሪፎርምና በተገኙ ተጨባጭ ውጤቶች ያላቸውን አድናቆትም መግለፃቸውን አመላክተዋል፡፡