የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ ህብረት በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ ገለፀ

By Mikias Ayele

March 24, 2025

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ህብረት በሶማሊያ ሰላም፣ መረጋጋት እና ልማት እንዲኖር የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋገጠ፡፡

በሶማሊያ የሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት አዲሱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሞሀመድ አሊ ዩሱፍ  ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሙሐመድ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ውይይቱን አስመልክተው የኮሚሽኑ ሊቀመንበር በኤክስ ገፃቸው እንዳስታወቁት÷ በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን እንዲሁም ቀጠናዊ ትስስርን ለማጠናከር እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን አድንቀዋል፡፡

ኃላፊነታቸውን ከተረከቡ በኋላ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን በሞቃዲሾ ያደረጉት ሊቀመንበሩ÷ የአፍሪካ ህብረት በሶማሊያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን መስራች እና አባል ሀገር እንደመሆኗ፣ ለአህጉራዊ አንድነት፣ አብሮነት እና የባለብዙ ወገን ትብብሮች ያላትን ቁርጠኝነት አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሙሐመድ በበኩላቸው÷ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር በሞቃዲሾ ጉብኝት በማድረጋቸው አድናቆታቸውን ገልጸው፤ በሶማሊያ እና በአፍሪካ ህብረት መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር ላሳዩት ተነሳሽነት ምስጋና ማቅረባቸውን ኬቢሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡

በተመሳሳይ ሞሀመድ አሊ ዩሱፍ ወደ በሶማሊያ የተሰማራውን የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሀይል የጎበኙ ሲሆን፤ ሰላም አስከባሪ ሀይሉ የሶማሊያን ሰላም ለመመለስ በርካታ መስዋዕትነት መክፍሉን አንስተዋል፡፡

ህብረቱ ሰላም አስከባሪ ሀይሉ ተልዕኮውን ለመፈፀም በሚንቀሳቀስበት ወቅት የሚያጋጥሙትን ችሮች ለመፍታት እና የሰራዊቱን አቅም ለማጎልበት ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡

በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሀይል ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ሰራዊታቸውን ማሰማራታቸው ይታወቃል።

በሚኪያስ አየለ