Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሀገሪቱን ዕድገት የሚመጥን የኃይል መሰረተ ልማት ግንባታ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገቱን የሚመጥን የኃይል መሰረተ ልማቶችን ግንባታ እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የተቋሙ የኮሙኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን እንዳሉት፤ አሁን ላይ ያለውን ሀገራዊ ኃይል የማመንጨት አቅም ከእጥፍ በላይ ለማሳደግ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ አምስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ነው፡፡

የሚገነቡ የማከፋፈያ ጣቢያዎችና የማስተላለፊያ መስመሮች እስከ አሁን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ያልነበሩትን አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግን ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የኃይል ተደራሽነት ሽፋኑን አሁን ካለበት 54 በመቶ ወደ 78 በመቶ ለማድረስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ማለታቸውን የተቋሙ መረጃ አመላክቷል፡፡

የሀገር ውስጥ የኃይል ፍላጎትን ከማሟላት ባሻገርም በቀጣናው የሚገኙ የጎረቤት ሀገራትን በኃይል ለማስተሳሰር በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በዚህም ለጅቡቲ፣ ኬኒያ እና ለሱዳን ኃይል እየቀረበ መሆኑንና በቅርቡም ለታንዛኒያ ማቅረብ እንደሚጀመር ጠቁመዋል፡፡

እየተገነቡ ያሉ የኃይል መሰረተ ልማቶች የአፍሪካ ህብረት በአጀንዳ 2063 የቀረፀውን አህጉሩን በመሰረተ ልማት የማስተሳሰር ዕቅድ ለማሳካት ጉልህ ድርሻ እንደሚያበረክቱም አመላክተዋል፡፡

ተቋሙ በአሁኑ ወቅት በኦፕሬሽን ላይ ብቻ የሚገኙ 194 የማከፋፈያ ጣቢያዎች፣ 20 ሺህ 673 ኪሎ ሜትር የማስተላለፊያ መስመሮች እና 17 የማመንጫ ጣቢያዎችን እያስተዳደረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

Exit mobile version