አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ያዘጋጁት የአምስት ዓመት የፍልሰት የጋራ ስትራቴጂክ ዕቅድና እና ብሔራዊ ኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ይፋ ሆነ፡፡
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት÷ መንግሥት ለፍልሰተኞች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እና ፍልሰት የሚያመጣቸውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል።
የአምስት ዓመት የፍልሰት የጋራ ስትራቴጂክ ዕቅድና እና ብሔራዊ ኮሙኒኬሽን ስትራቴጂም የኢትዮጵያ የፍልሰት አሥተዳደርን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አቢባቱ ዋኔ በበኩላቸው፤ ዕቅዱ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን የሚቀንስና መደበኛ ፍልሰትን የሚያበረታታ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተግበራዊ የሚደረገው ዕቅድ ውጤታማ እንዲሆንም ድርጅቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
ዕቅዱ የኢትዮጵያ የፍልሰት አሥተዳደርን ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ፣ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከልና ለተጎጅዎች ጥበቃና እንክብካቤ ለመስጠት፣ ውጤታማ የተመላሽ ፍልሰተኞች መረጃ አያያዝ ሥርዓትን ለማሻሻል የሚያግዝ ነው ተብሏል።
በቅድስት አባተ