የሀገር ውስጥ ዜና

ፖሊሲው ግቡን እንዲያሳካ በተሟላ መንገድ መተግበር እንዳለበት ተመላከተ

By Mikias Ayele

March 26, 2025

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ከፌደራል ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ በተሟላ መንገድ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ተመላከተ፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ላይ ያተኮረ ውይይት እያካሄደ ነው፡፡

በዚሁ ወቅት አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ከመጣው የሕዝብ ቁጥር ጋር የተመጣጠነ ምርታማነትን በማስመዝገብ ግብርናው በኢኮኖሚው ጉልህ ድርሻ እንዲኖረው የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡

ፖሊሲው በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ከመጣው የሕዝብ ቁጥር ጋር የተመጣጠነ ምርታማነትን በማስመዝገብ፤ የገጠር መወዋቅራዊ ሽግግርን በማሳካት፣ የተፈጥሮ ሃብትን በመጠበቅና በዘላቂነት በመጠቀም ግብርናው ለኢኮኖሚው ጉልህ ድርሻ እንዲያበረክት ያስችላል ተብሏል።

ላለፉት 22 ዓመታት በሥራ ላይ የነበረው ፖሊሲ በአዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ከተቀየረበት ምክንያቶች መካከል፤ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ፣ የፋይናንስ/ካፒታል ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት፣ የሕግ ማዕቀፎች ውስንነት መፍታትና የአርሶና አርብቶ አደሮችን ማበረታቻ ማካተት የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ፖሊሲው የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካም ከፌደራል ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ በተሟላ መንገድ ተግባራዊ መደረግ ይኖርበታል ነው የተባለው፡፡

በመጨረሻም የግብርና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ፖሊሲውን ለሁሉም የግብርና ተዋንያን በበቂ ሁኔታ ማስገንዘብ ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ እንደሚገኙም ተገልጿል።

በደሳለኝ ቢራራ