አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም በመቻል ከተረጅነት ለመላቀቅ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።
ባለፋት ሥድስት ወራት ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመቻል የተሠሩ ሥራዎች በተገመገመበት መድረክ ላይ ርዕሰ መሥተዳደሩ እንዳሉት፤ በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ የሚፈጠሩ ችግሮችን በራስ አቅም ለመቋቋም የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡
ከተረጅነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ እና ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመቻል የእህል ክምችትን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመቻል የተከናወኑ ተግባራትም ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ምርት እና ምርታማነትን በይበልጥ በማሳደግ ራስን በምግብ ለመቻል፣ የእህል ክምችትን ለማሳደግ በዞን እና በወረዳዎች በስፋት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በዘርፉ የሚከናወኑ ሥራዎችም ሕዝባዊ መሰረት እንዲኖራቸው አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።