አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀላባ ቁሊቶ ክላስተር ማዕከል የክልል መሥሪያ ቤቶች አፈጻጸም የሚገኝበት ደረጃ መለየትን ታሳቢ ያደረገ መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር እንዳሻው ጣሰውን (ዶ/ር) ጨምሮ የፍትሕ እና የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች አመራሮችና ማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል፡፡
የሁለቱም ቢሮዎች የዋና ዋና ዕቅዶች አፈጻጸም ሪፖርት በመድረኩ የቀረበ ሲሆን፤ የቀጣይ ጊዜ የትኩረት መስኮችም ተመላክተዋል።
ርዕሰ መሥተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ሴክተሮቹ በሁሉም መስኮች አዳጊ መሻሻሎችን እያሳዩ ነው፤ የክትትልና ድጋፍ ሥርዓቱም እየተጠናከረ ይገኛል፡፡
ተግባራትን በጠራ ዕቅድና በእውቀት ለመምራት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ማሳሰባቸውን የርዕሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይም የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡