አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደብረብርሃን፣ ሱሉልታ እና ቢሾፍቱ ከተሞች የመካከለኛ መስመር የመልሶ ግንባታና ማሻሻያ ፕሮጀክት ግንባታ ስምምነት ተፈረመ፡፡
እነዚህ ከተሞች በቀጣይ ለመገንባት በዕቅድ የተያዙ የ10 ከተሞች የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ማሻሻያና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት አካል መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የፕሮጀክት ግንባታ ስምምነቱ የተከናወነው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና በጋናው ዊልኪንስ ኢንጅነሪንግ ኩባንያ መካከል ነው፡፡
ከዓለም ባንክ በተገኘ 17 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር ብድር የሚከናነው ይህ ፕሮጀክት፤ በሁለት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መረጃ አመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጌቱ ገረመው (ኢ/ር) እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ በከተሞቹ ያለውን የኤሌክትሪክ አቅርቦት አስተማማኝ በማድረግ ደንበኞች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ያግዛል፡፡
የዊልኪንስ ኢንጅነሪንግ ኩባንያ ተወካይ ኦማን ፍሪምፖንግ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱን በተያዘው ጊዜና የጥራት ደረጃ አጠናቅቀው እንደሚያስረክቡ አረጋግጠዋል፡፡
የመልሶ ግንባታ ሥራው 386 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ መስመር እንደሚሸፍን እና 315 ኪሎ ቮልት አምፒር አቅም ያላቸው 87 አዲስ ትራንስፎርመሮች እንደሚተከሉ ተገልጿል፡፡
ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የኤሌክትሪክ የመቆራረጥ ድግግሞሹን 45 በመቶ እና የቆይታ ጊዜውንም በ50 በመቶ እንደሚቀንስ ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም የእንጨት ምሶሶዎችን ወደ ኮንክሪት መቀየር፣ ያልተሸፈነ የኤሌክትሪክ መስመርን በተሸፈኑ ገመዶች የመቀየር ሥራ እንደሚሰራ ነው የተገለጸው፡፡