አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከለውጡ ወዲህ በክልሉ የተሠሩ መሠረተ ልማቶች የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጣቸውን ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያነጋገራቸው የሶማሌ ክልል ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
በክልሉ በርካታ መሠረተ ልማቶች እየተከናወኑ መሆኑን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፤ ይህም ከዓመታት በፊት ሲነሳ የነበረውን የልማት ጥያቄ መልሷል ብለዋል፡፡
በተለይም ከለውጡ ወዲህ ለክልሉ የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንገድ እና የንጹህ መጠጥ ውኃን ጨምሮ ሌሎች መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በከተሞች ከተከናወኑ መሠረተ ልማቶች ባለፈ፤ የአርብቶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ የሚቀይሩ የመስኖ ፕሮጀክቶች ክልሉ አምራች እንዲሆን አስችሎታል ነው ያሉት፡፡
የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መሀመድ አደን በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም በፖለቲካ ተሳትፎ በአጋርነት ሲታይ የነበረ ክልል ከለውጡ በኋላ በሀገር ጉዳዮች ላይ እኩል ተሳትፎ እያደረገ ያለበት ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡
ከልማት አንጻር አሁን ላይ በክልሉ የሚታረሰው መሬት ከለውጡ በፊት ከነበረበት 350 ሺህ ሔክታር ወደ 970 ሺህ ሔክታር ከፍ ማለቱን ጠቁመዋል፡፡
በታሪኩ ለገሰ