አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመንግሥትን የበጀት አጠቃቀም ሥርዓት ውጤታማ የሚያደርግ አሠራር ተግባራዊ ሊደረግ እንደሆነ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
አሰራሩ በተለያዩ መንገዶች መንግስት የሚያገኛቸውን ገንዘቦች ወደ አንድ ቋት ለመሰብሰብ የሚያስችል እና ለታለመለት አገልግሎት እንዲውል የሚያስችል ‘የትሬዥሪ ነጠላ አካውንት አሠራር’ መሆኑ ተገልጿል።
ይህም መንግሥት ያለውን የገንዘብ መጠን ማወቅ እንደሚያስችለው የተገለጸ ሲሆን፤ ገንዘብን የመያዝ እና የማስተዳደር ሂደትን በአንድ ማዕከል እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑ ተመላክቷል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) አሠራሩ ዘመናዊ የገንዘብ አሥተዳደር ሥርዓት የሚፈጥር መሆኑን ገልጸው፤ የቁጥጥር ስራውን ውጤታማ የሚያደርግ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
በተለያዩ የሒሳብ ቁጥሮች የተበታተነውን የመንግሥት ገንዘብ ወደ አንድ የሚያመጣም አሰራር እንደሆነ ገልጸው፤ በቀዳሚነት በፌደራል መንግስት ደረጃ ተግባራዊ መደረግ እንደሚጀምር አመልክተዋል።
ይህ አሠራር በቀጣይ ወደ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች እንደሚወርድ ጠቁመው፤ ለተግባራዊነቱና ውጤታማነቱ የሚመለከታቸው ሁሉ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በሰለሞን ይታየው