አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግናን ዕውን ለማድረግ በሚከናወኑ ተግባራት ተሳትፎውን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ገለጹ።
1 ሺህ 446ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል በድሬዳዋ ከተማ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ተከብሮ ተጠናቅቋል፡፡
ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በዚህ ወቅት ÷ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግናን ዕውን ለማድረግ አበረታች ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡
ሙስሊሙ ማህበረሰብ ተሳትፎውን ወደ ላቀ ደረጃ በማሳደግ ዘላቂ ሰላምና ዕድገት ለማፅናት ይበልጥ መስራት እንደሚጠበቅበት ጠቁመው÷ በረመዳን ፆም የታዩት የመረዳዳትና የመደጋገፍ ተግባራት በቀጣይም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የድሬዳዋ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ አብዱላሂ መሐመድ በበኩላቸው÷ በዓሉን ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳት እና የታመሙትን በመጠየቅ መሆን ይኖርበታል ብለዋል።
በዓሉ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት እንዲሆን ተመኝተው÷ ህዝበ ሙስሊሙ በድሬዳዋ ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ ውስጥ እያበረከተ የሚገኘውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡