አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ቅርሶች ጠብቆ ለማቆየት የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር አስታውቋል፡፡
የዩኔስኮ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ተወካይ ሪታ ቢሶናውት (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ በርካታ ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት ማስመዝገቧን አውስተዋል፡፡
በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ተጨማሪ ቅርሶችን ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።
የቅርሶች በዩኔስኮ መመዝገብ ቅርሶችን ለመንከባከብና ለመጠበቅ እንዲሁም የሚጎበኙ ሰዎችን ቁጥር በመጨመር የአካባቢው ማህበረሰብ የቱሪዝም ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ሃብቶችን ለዓለም ማህበረሰብ የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሰራ ጠቅሰው÷ በኢትዮጵያ ያሉ ዲፕሎማቶች በሀገሪቱ ያሉ ቅርሶችን እንዲጎበኙ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።