አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፖለቲካዊ ችግሮቻችንን በጋራ እንፍታ የሚል የመሪ ጥሪ ሲቀርብ የታየው በዚህ የለውጥ ጊዜ ነው ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ዓለም አቀፍና የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) የለውጡ መንግሥት የመጣበትን ሰባተኛ ዓመት በተመለከተ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ሀገራዊ ለውጡ ዜጎችን ወደ ፊት ያመጣና ተሣትፏቸውን ከፍ ያደረገ እንዲሁም የፖለቲካ ባይተዋርና ባለቤት የሚለውን ክፍፍል ያስቀረ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለውጡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገራዊ ጉዳይ ያገባዋል የሚለውን ዕሳቤ ማምጣቱን ገልጸው÷ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን የሀገሪቱን የፖለቲካ ችግር ለመፍታት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ የቀረበበት እንደሆነም አብራርተዋል።
እንዲሁም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስብራት ለመጠገን በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ግንባር ቀደም ተሣታፊ እንዲሆኑ የተደረገው ጥሪ ትልቁ ጥሪ ነው ሲሉም አክለዋል።
በዚህም ለዓመታት ኑሯቸውን በውጭ ያደረጉና ለሀገራቸው ባይተዋርና የነበሩ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲገቡና እንዲደራጁ፣ በሚመቻቸውና በሚፈልጉ የፖለቲካ አደረጃጀት እንዲሰለፉ እንዲሁም ለሀገራቸው ዕድገት ሐሳባቸውን እንዲያዋጡ የተደረገው ጥሪ ትልቅ ለውጥ መሆኑንም አስታውሰዋል።
በተለያዩ ሀገራትና ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ፊት የመጡበት፣ መደራጀት፣ ቢሮ መክፈት እንዲሁም ሐሳቦቻቸውን ወደ ሕዝብ ማቅረብ የጀመሩበት ወቅት መሆኑንም አንስተዋል።
ይህም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ትልቅ ለውጥ እንደሆነ አመላክተዋል።
በአድማሱ አራጋው