አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብርቱካን ተመስገንን በተመለከተ በመገናኛ ብዙኃን ከተላለፈው ሐሰተኛ ዘጋቢ ፊልም ጋር በተያያዘ በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ለፖሊስ ተጨማሪ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ፡፡
ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ ተጨማሪ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ የሰጠባቸው ተጠርጣሪዎች፤ ብርቱካን ተመስገን፣ ነብዩ ጥዑመልሳን የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ፣ ታሪኩ ኃይሌ የአዲስ ምራፍ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ፣ ደረጀ ሉቃሌ፣ ኅሊና ታረቀኝ፣ ንጥር ደረጀ እና መታገስ ዓለሜ ናቸው፡፡
በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል ስልጣንን በኃይል ለመያዝ ፣ የጦር መሣርያ በመታጠቅ፣ በሕገ-ወጥ መንገድ በመደራጀት፣ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሰ ከሚገኘው ጽንፈኛና ፀረ ሰላም ቡድን አመራሮች ጋር በጥቅም በመመሳጠር፣ መንግሥት የሕዝብ ተቀባይነት እንዲያጣና ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ እንዲደረግበት በማሰብ፣ ተዋድደውና ተከባብረው በሚኖሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መካከል ቅራኔ በመፍጠርና ወደ ግጭት እንዲገቡ ለማድረግ፣ በውጭ ሀገር ከሚገኝ የፀረ ሰላም የቡድኑ አመራሮች ጋር በተለያዩ መገናኛ መንገዶች በመገናኘት እና ተልዕኮ በመቀበል የሥራ ባህሪያቸውን እንደመልካም አጋጣሚ መጠቀም የሚሉ የምርመራ የጥርጣሬ መነሻውን ለችሎቱ አቅርቧል፡፡
ፖሊስም የምርመራ ሥራየን በሰውና በሠነድ ማስረጃ በስፋት ማጣራት እንድችል 14 ተጨማሪ ቀናት ይፈቀድልኝ ሲል ባሳለፍነው ዓርብ መጠየቁን ተከትሎ፤ ፍርድ ቤቱ በዛሬው ዕለት የፖሊስን ጥያቄ በመቀበል 14 የምርመራ ቀን ፈቅዷል፡፡
በተጨማሪም እስከ አሁን በተጠርጣሪዎቹ ላይ ያሰባሰበውን መረጃና ቀሪ የምርመራ ሥራ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት አቅርቧል።
በሲፈን መኮንን