አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘመናዊ እና ከፍተኛ የስራ አቅም ያላቸው የኮምፒውተሮች ድጋፍ አደረገ፡፡
ዛሬ የአስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች በፋና ዋናው መስሪያ ቤት በመገኘት ያደረጉት ድጋፍ የሁለቱን ተቋማት መልካም ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያግዝ ነው።
በድጋፍ አሰጣጥ መርሐ ግብሩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪና የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ለሚዲያዎች ድጋፍ ሲያደርግ የመጀመሪያው እንዳልሆነ አንስተዋል።
ዘመኑ የዲጂታል በመሆኑ ፋናን ለማዘመን እና ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር እንዲጓዝ የተሰጠው ድጋፍ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዳንኤል ጉታ በበኩላቸው ሁለቱ ተቋማት በትብብር ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ ተቋማቸው ያደረገው ድጋፍ የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የዲጂታል ሚዲያ ዘርፉን እንቅስቃሴ ይበልጥ ለማዘመን እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ተቋማቸው በቀጣይም ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በተለያዩ ዘርፎች በጋራ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አድማሱ ዳምጠው ÷ ለፋና ስለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ የተቋማቱ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በወንድማገኝ ፀጋዬ