አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መጋቢት 24 ኢትዮጵያ ሁለት ታሪካዊ እጥፋቶችን የተጎናጸፈችበት ዕለት ነው ሲሉ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ርስቱ ይርዳው ገለጹ፡፡
የአገልግሎቱ አመራሮችና ሠራተኞች ሀገራዊ ለውጡ ዕውን የሆነበትን ሰባተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ፤ “ትናንት፣ ዛሬና ነገን ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል መሪ ሐሳብ በፓናል ውይይትና በደም ልገሳ አስበዋል፡፡
አቶ ርስቱ በዚሁ ወቅት፤ መጋቢት 24 ኢትዮጵያ ሁለት ታሪካዊ እጥፋቶችን የተጎናጸፈችበት ዕለት ነው ማለታቸውን ተቋሙ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የላከው መረጃ አመላክቷል፡፡
በቁጭት ሲነሳ የነበረው የዓባይ ወንዝን የመጠቀም መብት የሕዳሴ ግድብን መሰረት በመጣል ዕውን ተደርጓል ያሉት አቶ ርስቱ፤ በዚህም ከኢትዮጵያውያን አልፎ በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ተጨማሪ የይቻላል መንፈስን የተከልንበት ዕለት ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዛሬ ሰባት ዓመት በታሪኳ ያለምንም ደም አፋሳሽ ግጭት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በማድረግ አካታችና አቃፊ የፖለቲካ ሥርዓት እውን ያደረገችበት ዕለት ሌላኛው የታሪክ እጥፋት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በለውጡ ዓመታት በየዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል እንደ ተቋም የተሰጠንን የሀገር ደኅንነትና ብሔራዊ ጥቅምን የማረጋገጥ ተልዕኮ ለማሳካት ሁሉም በቁርጠኝነት ሊሠራ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎችም ባለፉት የለውጥ ዓመታት በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና በማኅበራዊ ዘርፎች ስኬቶች መመዝገባቸውን ያነሱ ሲሆን፤ በመረጃና በጸጥታ ተቋማት ሰፊ የሪፎርም ሥራዎች መከናወናቸውም ተጠቅሷል፡፡
በተለይም በተቋሙ በተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች አገልግሎቱ የጠራ ተልዕኮ እንዲኖረው ተደርጓል መባሉን መረጃው አመላክቷል፡፡
የሰው ኃይልን በማጠናከር፣ በቴክኖሎጂ በማዘመን፣ አደረጃጀትና አሠራርን በማሻሻል ስኬታማ ሥራዎች መከናወናቸውም ተብራርቷል፡፡
ባለፉት የለውጥ ዓመታት እንደ ሀገር ውስብስብ ችግሮችን በመጋፈጥ አኩሪ ድሎችን ማስመዝገብ ቢቻልም፤ አሁንም ያልተሻገርናቸው ፈተናዎች አሉ ብሏል መረጃው፡፡
ሁለንተናዊ ሰላምን ማረጋገጥ፣ ነፃነትን ማስተዳደር መቻል፣ ድህነትና ኋላ-ቀርነትን ማስወገድ፣ ሕዝብን የሚያረካ አገልግሎት ማቅረብ በቀጣይ በትኩረት መከናወን ያለባቸው ትልሞች መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡