አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብርሸለቆ መሠረታዊ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በዛሬው ዕለት መሰረታዊ ወታደሮችን አሥመርቋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሃመድ ተሰማ፤ የመከላከያ ሃይል ውጤታማ ግዳጆችን እንዲወጣ ለማስቻል ዘርፈ ብዙ ተግባራት መሠራቱን ገልፀዋል።
የውትድርና ሙያ ክቡርና ውድ ህይወትን ሰውቶ ሀገርን ማፅናት፣ ህዝብን ማገልገል የሚጠይቅ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ይህን ሙያ በጥብቅ ዲስፕሊን ለመፈጸም ደግሞ መሰልጠን፤ ሙያው የሚጠይቀውን እውቀት፣ ብቃት፣ ችሎታ፣ መፍጠርና በስነ-ልቦና መዘጋጀት የግድ አስፈላጊ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የ41ኛ ዙር ተመራቂዎች በውትድርና ሙያ ሀገራችሁንና ህዝባችሁን በፍፁም ታማኝነት ለማገልገል ፈቅዳችሁ፣ ሰልጥናችሁ ወደ ተቋሙ የተቀላቀላችሁ የጀግና ህዝብ ልጆች ስለሆናችሁ ልትኮሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ተመራቂዎች ከነባሩ ሠራዊት የሚያገኙትን ልምድና ተሞክሮ ጨምረው በየጊዜው ብቃታቸውን በማሳደግ የሚሰጣችቸውን ህገ-መንግስታዊ ተልዕኮ ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ሠራዊቱ የተገነባባቸውን እሴቶችና ህዝባዊ ባህሪን ተላብሳችሁ በጀግንነት፣ በታዛዥነትና በፅኑ ዲስፕሊን ልትመሩ ይገባል ማለታቸውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አመላክቷል።