አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ለጣና ፎረም እየተደረገ ያለውን ዝግጅት በተመለከተ ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ጋር በባህር ዳር ከተማ ተወያዩ፡፡
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት፤ የክልሉ መንግስት ለፎረሙ ያደረገውን ዝግጅትና የከተማዋን መሰረተ ልማት በማዘመን ላከናወናቸው ተግባራት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
አቶ አረጋ ከበደ በበኩላቸው፥ የክልሉ መንግስት ባለፉት ዓመታት በርካታ ሁነቶችን በስኬት ማስተናገዱን ገልጸው፥ የባህር ዳር ከተማ መሰረተ ልማትና ተስማሚ የአየር ሁኔታ የተለያዩ ጉባኤዎችን ለመሳብ እንደሚያስችል አንስተዋል፡፡
የጣና ፎረም በአፍሪካ ሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን በማድረግ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፥ ዘንድሮ 11ኛው ፎረም እንደሚካሄድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡