የሀገር ውስጥ ዜና

የጁገል ግንብ እድሳት ታሪካዊውን ቅርስ ይበልጥ ውበት አጎናጽፎታል ተባለ

By Yonas Getnet

April 03, 2025

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጁገል ግንብ እድሳት ታሪካዊውን ቅርስ ይበልጥ ውበት እንዲጎናፀፍ አስችሎታል ሲሉ የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ነዋሪዎቹ እድሜ ጠገቡ የጁገል ግንብ እድሳት ሳይደረግለት በርካታ ዓመታትን በማስቆጠሩ የቅርሱ ውብ ገፅታ ደብዝዞ ነበር ብለዋል።

ይሁንና ሀገራዊ ለውጡ ዕውን በሆነ ማግስት ለዚህ ታሪካዊ ቅርስ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲታደስ እና ይበልጥ እንዲለማ መሰራቱን ገልጸዋል።

የጁገል ግንብ እድሳት ታሪካዊውን ቅርስ ይበልጥ ውበት እንዲጎናፀፍ በማድረጉ በርካታ ቱሪስቶችን ለመሳብ የሚያስችል ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

የሐረሪ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ተወለዳ አብዶሽ ቅርሱን ለማደስ በተደረገ የመጀመርያ ዙር እርምጃ ከ6 ሺህ 100 ሜትር ስኩዌር በላይ የሆነ ስፍራ አረንጓዴ እንዲለብስ መደረጉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ማስፋት፣ የጁገል ዙርያ የኮሪደር ልማት ስራዎችን መከወን፣ ታሪካዊ ቅርሶችን ማደስን ጨምሮ ሌሎች ሥራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል።

ቅርሱን የማደስ ሥራ አሁንም የሚከወን መሆኑን ጠቅሰው፤ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ የጋራ ጥረት 5 ነጥብ 1 ኪሎሜትር አዲስ የኮሪደር ልማት ስራ በዙርያው እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በሐረሪ ክልል ያሉ በርካታ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራ የሆኑ ሙዚዬሞች ታሪካዊነታቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ ቅርሶቹን የማደስ ሥራ ትኩረት እንደተሰጠውም ተናግረዋል።

በታምራት ደለሊ