Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በእግር ኳስ ህይወቱ ቀይ ካርድ ያለተመለከተው ኢኔሽታ …

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከስፔኑ ክለብ ባርሴሎና ላማስያ አካዳሚ በመነሳት እልፍ አእላፍ ስኬቶችን የተጎናፀፉ አሉ።

እንደእነ ሊዮኔል ሜሲ፣ ዣቪ ሄርናንዴዝ እና ሰርጂዮ ቡስኬት የመሳሰሉ ተጨዋቾች በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።

ስፔናዊው የባርሴሎና የቀድሞ የመሀል ሜዳ ተጫዋች አንድሬስ ኢኔሽታም ከዋነኞቹ አንዱ ነው።

በተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች ጭምር ትልቅ ክብር ስለሚሰጠው ኢኔሽታ በአንድ ወቅት የቀድሞ የማንቼስተር ሲቲ ተጨዋች ዴቪድ ሲልቫ “ብዙ ጊዜ ሜሲ ወይም ሮናልዶ ምርጡ እንደሆነ ይጠይቁኛል፥ ነገርግን ለእኔ  ኢኔሽታ ቁጥር አንድ ነው” ሲል አድናቆቱን ገልጾለታል።

የቡድን አጋሩ ዣቪ ሄርናንዴዝ ደግሞ “ኢኔሽታ ማለት በቀላሉ የስፔን ሙሉ ተጫዋች ማለት ነው፤ እሱ የተሟላ ብቃት ስላለው ጨዋታ እንዳይከብድ ያደርጋል” ሲል ተደምጧል።

ስፔናዊው ኮከብ አንድሬስ ኢኔሽታ ኳስ ይነጥቃል፣ ሜዳ ሙሉ ያለመታከት ይሮጣል፣ በአንድ ሁለት ቅብብል የተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል ይደርሳል።

የተሟላ ብቃቱ እግር ኳስ ካሳየችን ድንቅ አማካዮች መካከል አንዱ አድርጎታል።

ለዚህ ደግሞ ደቡብ አፍሪካ ያስተናገደችው የፈረንጆቹ 2010 የዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ምስክር ነው።

በዚህ ጨዋታ ላይ የኔዘርላንድስ ብሔራዊ ቡድን አርያን ሮበን እና ቫንፔርሲን ጨምሮ ሌሎችንም ተጫዋቾች ሲያሰልፉ፤ ስፔን ደግሞ ከግብ ጠባቂው ኢከር ካስያስ ጀምሮ ሰርጂዮራሞስ፣ ፑዮል፣ ፒኬ፣ ዣቪ፣ ኢኔሽታ እና ፋብሪጋስን የመሳሰሉ ኮከቦችን በቋሚ 11 ውስጥ አካታለች።

ጨዋታው በመደበኛ ሰዓት ግብ ሳይቆጠርበት በጭማሪው ሰዓት ተሽለው የቀረቡት ስፔኖች በ116ኛው ደቂቃ ላይ በአንድሬስ ኢኔሽታ አማካኝነት ባስቆጠሯት ግብ የዓለም ዋንጫን ማሳካት ቻሉ።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የዓለም መገናኛ ብዙሀን ስለ ስፔናዊው የባርሰሎና ኮከብ አንድሬስ ኢኔሽታ በሰፊው ዘገቡ።

የ2010 የባሎንዶር ሽልማትንም ያገኛል ተብሎ ሲጠበቅ የቡድን አጋሩ ሊዮኔል ሜሲ የክብሩ ባለቤት ሆነ።

ይህ ጉዳይም ብዙዎችን አሳዘነ፤ አንዳንዶችም በሽልማቱ ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው አደረገ።

ነገር ግን ስፔናዊው ኮከብ ዝምታን በመምረጥ እግር ኳስን የሚጫወተው የግል ሽልማት ለማግኘት ሳይሆን የኳስ ፍቅር እና ፍላጎት በልቡ ውስጥ ሰርፆ በመግባቱ እንደሆነ አሳየ።

በፈረንጆቹ 1984 ስፔን ውስጥ በምትገኘው አነስተኛ ከተማ ፉንቴል ቢላ የተወለደው ኢኔሽታ፤ ላማሲያን የተቀላቀለው በ12 ዓመቱ ነበር፡፡

ስፔናዊው ኮከብ አንድሬስ ኢኔሽታ እግር ኳስን እስከተሰናበተበት ጊዜ ድረስ በርካታ ታሪኮችን የፃፈ ሲሆን በእግር ኳስ ህይወቱ ከአንድ ሺህ በላይ ጨዋታዎችን አድርጎ አንድም ቀይ ካርድ አልተመለከተም።

በወንድማገኝ ፀጋዬ

Exit mobile version