አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 4ኛው የኢትዮ-ኡጋንዳ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከርና በተለያዩ ዘርፎች ስምምነቶችን ለመፈፀም ያለመ ነው ተብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በነበሩ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባዎች ላይ የተደረሱ ስምምነቶችን ስትተገብር መቆየቷን ተናግረዋል።
በቀጣናው ሽብርተኝነትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረትና የዓባይ ወንዝ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ ያለው ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል የሚችልባቸው አማራጮች በመድረኩ ላይ እንደሚነሱም ጠቁመዋል።
የኡጋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦዶንጎ ጄጄ አቡበከር ሁለቱ ሀገራት በንግድ፣ በግብርና፣ በመሠረተ ልማትና በትራንስፖርት ዘርፍ በጋራ መስራት የሚያስችላቸው ዕድሎች መኖሩን አብራርተዋል።
በስብሰባው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ የሀገራቱ ዲፕሎማቶችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በአሸናፊ ሽብሩ