አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ የዲፕሎማቲክ ማዕከልነቷን የሚያረጋግጡ ስራዎችን ሰርታለች ሲሉ የፓን አፍሪካ ወጣቶች አመራር ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለጹ።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው የፓን አፍሪካ ወጣቶች አመራር ጉባኤ ተሳታፊ የወጣት ዘርፍ ሚኒስትሮች የአዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ማዕከል እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን ጎብኝተዋል።
ሚኒስትሮቹ ኢትዮጵያ አሁንም ለአፍሪካ ስልጣኔ አስተዋፅኦ ማበርከቷን እንደቀጠለች ገልጸው፤ በተለያዩ መስኮች እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ ለሌሎችም ሀገራት ምሣሌ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።
በጉብኝታቸው የተመለከቷቸው አዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የኢትዮጵያ የአህጉሩ አረዓያነት ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በተቋማቱ ባዩት ነገር መደነቃቸውን ገልፀዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ስኬታማ ጉባኤን ለማካሄድ የሚያስችል አቅም እንዳላት እንደተገነዘቡ ገልፀው፤ አዲስ አበባ የዲፕሎማቲክ ማዕከልነቷን የሚያረጋግጡ ስራዎችን መስራቷን እንደተመለከቱ መናገራቸውን የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።