አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን እና የኡጋንዳን የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንሰራለን ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
ዛሬ በተካሄደው 4ኛው የኢትዮጵያ እና የኡጋንዳ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ የሁለቱ ሀገራት ቀጣይ የትብብር መስኮች ተለይተው፤ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈርሟል።
ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ በጋራ ኮሚሽን ስብሰባው በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የትብብር ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት ተደርጓል።
ሀገራቱ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በፖለቲካዊ ዘርፎች ትብብርን የሚያጠናክር ስምምነት መፈራረማቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ስምምነቱ የጋራ ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግር ገልጸው፤ የትብብር ስምምነቱ ግቡን እንዲመታ ኢትዮጵያ አበክራ ትሰራለች ሲሉ ገልጸዋል።
የኡጋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦዶንጎ ጄጄ አቡበክር በበኩላቸው፤ የኡጋንዳ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በህዝብ ለህዝብ የተሳሰረ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ነው ያረጋገጡት።
በፖለቲካ፣ በድንበር ተሻጋሪ የውኃ ሀብት አጠቃቀም፣ በኢነርጂ፣ በንግድ እና በቀጣናዊ ሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር፤ የበረራ አገልግሎት ስምምነት እና ሌሎች ግንኙነቱን የበለጠ የሚያጠናክሩ ሰባት የመግባቢያ ስምምነቶችን መፈራረማቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።