አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ችግሮችን በሀይል ለመፍታት መሞከር ዘላቂ መፍትሔን አያመጣም ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ገለጹ፡፡
ኮሚሽኑ በአማራ ክልል የሚያከናውነው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት በባህር ዳር ዩንቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።
ዋና ኮሚሽነሩ በዚሁ ወቅት፥ በኢትዮጵያ ያሉ ያለመግባባት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት መመካከር አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ፥ በቀጣይ ቀናት በሚኖረው ምክክር ሀላፊነት በተሞላበት መንገድ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የሀሳብ ልዩነቶችን በሀይል ለመፍታት በተደረጉ ግጭቶች የአማራ ህዝብ ዋጋ መክፈሉን የጠቆሙት ዋና ኮሚሽነሩ፥ ይህ ሁነት ሀገራዊ ምክክር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
መድረኩ በቀጣይ ለሚደረጉ የምክክር ምዕራፎች ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፥ ኮሚሽኑ አሁንም በክልሉ ትጥቅ ላነገቡ አካላት ወደ ምክክር እንዲመጡ ጥሪ ማድረጉን ይቀጥላልም ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን በአንድ ልብ መክረው በቆሙባቸው ጊዜያት ሁሉ የተነሱባቸውን ጠላቶች ድል መንሳታቸውን በማውሳት፥ ሀገራዊ ምክክሩንም በዚህ መንፈስ ከዳር ማድረስ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።