የሀገር ውስጥ ዜና

የለውጡ መንግስት ህዳሴ ግድብን ከአጣብቂኝ በማውጣት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ማድረስ ችሏል – አብርሃም በላይ (ዶ/ር)

By Hailemaryam Tegegn

April 05, 2025

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የለውጡ መንግስት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ፕሮጀክቱን ከአጣብቂኝ ውስጥ በማውጣት ለመጨረሻ ምዕራፍ ማብቃቱን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የግድቡን የኤሌክትሮ መካኒካል ስራዎች ለመስራት ሃላፊነት የተሰጠው ሀገር በቀል ተቋም ከፍተኛ የአቅምና የስነ-ምግባር ክፍተቶች ስለነበሩበት ፕሮጀክቱን አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቶት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ነገር ግን የለውጡ መንግስት ለፕሮጀክቱ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረትና ባሳየው የላቀ የመፈፀም ብቃት ግድቡ አሁን ለደረሰበት የመጨረሻ ምዕራፍ ለማብቃት ተችሏል ብለዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ ፕሮጀክቱን በ7 ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ሳሊኒ ከተባለ የጣሊያን ኩባንያ ጋር ውል ተፈራርሞ እንደነበር አብርሃም (ዶ/ር) አስታውሰዋል፡፡

በመቀጠልም ከሁለቱ ዓመታት በኋላ የግድቡ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራዎች ከዋናው ተቋራጭ ተወስዶ በመሰል የግንባታ ሂደት ልምድ ላልነበረው ለሜቴክ መሰጠቱን አንስተዋል፡፡

ለውጡ እውን ከሆነ በኋላ ቅድሚያ ተሰጥቶ በተከናወነው የመገምገም ስራ ፕሮጀክቱ ላጋጠሙት ችግሮች ዋነኛው ምንጭ ሜቴክ እንደነበር መለየቱንም ገልጸዋል፡፡

ከተለያዩ አካላት ጋር በተበጣጠሰ ሁኔታ የግንባታ ውሎች በመታሰራቸው የፕሮጀክቱን አፈጻጸም ለማወቅ አስቸጋሪ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡

እነዚህን ችግሮች በመፍታት የፕሮጀክት አስተዳደር ስርዓቱን በማስተካከል፣ የአመራር ለውጥ በማድረግና አቅም ካላቸው አዳዲስ ተቋራጮች ጋር ውል በማሰር ወደ ውጤት ለመምጣት የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

ግንባታው በለውጡ ማግስት 63 በመቶ አፈጻጸም ላይ የነበረ ቢሆንም፥ ወደ ኋላ በመመለስ በተሻለ ጥራት በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ ግድቡን በዚህ ዓመት መጨረሻ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ የቅርብ ክትትል በማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አብርሃም (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ