የሀገር ውስጥ ዜና

ዜጎች በደም እጦት ለጉዳት እንዳይዳረጉ ርብርብ እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ

By ዮሐንስ ደርበው

April 06, 2025

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዜጎች በደም አቅርቦት እጥረት ምክንያት ለከፋ ጉዳት እንዳይዳረጉ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ጥሪ አቀረቡ፡፡

የኢትዮጵያ ደምና ኅብረ-ኅዋስ ባንክ አገልግሎት ከጋምቤላ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት እና ከክልሉ ደም ባንክ ጋር በመተባበር በደምና ኅብረ-ኅዋስ ልገሳ ላይ ያተኮረ መድረክ አካሂዷል፡፡

ወ/ሮ ዓለሚቱ በዚሁ ወቅት በክልሉ የደም አቅርቦት ከፍላጎት ጋር የተጣጣመ አለመሆኑን ገልፀው፤ ደም መለገስ ሕይዎትን መታደግ በመሆኑ በዚህ በጎ ተግባር ላይ በንቃት መሳተፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ደምና ኅብረ-ኅዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ በበኩላቸው፤ ደም መለገስና ሌሎችም በዚህ ተግባር እንዲሳተፉ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡