አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም ትግበራ ስኬታማነት ሁሉም በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
“ልኅቀት በሰው ተኮር አገልግሎት” በሚል መሪ ሐሳብ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የፌዴራል ከፍተኛ የመንግሥት አመራር አባላት ተሞክሮ ተኮር ሥልጠና ተጠናቅቋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም ትግበራ አይቀሬ ስለሆነ ለስኬታማነቱ ሁሉም ትኩረት ሊሰጥ ይገባል።
የመንግሥት አገልግሎት የተሳካ እንዲሆንም ሁሉም አመራር የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸው፤ ሪፎርሙን ሕዝብ፣ መንግሥት እና ሲቪል ሰርቪሱም በእጅጉ የሚፈልገው መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ሀገር የተደራጁ ተቋማት ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን አውስተው፤ የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም ፈጥኖ መሣካት ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ሁሉም ክልሎች የሲቪል ሰርቪስ ግንባታ በፍጥነት እውን እንዲሆን ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመው፤ ለዚህም ዝግጁነታቸውን ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የተደራጀ የመንግሥት ሥርዓት ጅማሮ ከሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ጋር በማናበብ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የሪፎርሙ መሣካት በሀገር ደረጃ ለተጀመረው የተቋማት ግንባታ እውን መሆን ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም ገልጸዋል።
በመንግሥት እና ሕዝብ መካከል ያለው ጥምረትም ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል፡፡
የሪፎርሙ መሳካት ለተቋማት ግንባታ ትልቅ መሠረት የሚሆን ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ተቋማት ለሕዝቡ የሚሰጡትን አገልግሎት እንዲጨምሩ የሚያደርግ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በተጨማሪም ለሕዝቡ ፈጣን፣ ተደራሽ፣ አስተማማኝ እና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመሥጠት የሪፎርሙ ትግበራ ወሳኝ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
የተቋማትን ግንባታ ለመሳካት ሲቪል ሰርቪሱ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ ለተገልጋዩ እርካታ ያለው አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል አብራርተዋል፡፡
እንደ ሀገር የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም ለማሣካት የተደራጁ አግባቦች መኖራቸውንም ገልጸዋል።
የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርምን በመተግበር የማይናወጥ ሲቪል ሰርቪስ መገንባት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ የሪፎርሙን አተገባበር በተመለከተም ተመሣሣይ አቋም እና አቅጣጫ መከተል ይገባል ብለዋል፡፡
የለውጡ መንግሥት እስከ አሁን በርካታ የሪፎርም ተግባራትን ማከናወን መቻሉን አንስተው፤ አሁንም ይህንን ሪፎርም ውጤታማ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡
የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርምን የጀመሩ ተቋማት መኖራቸው ሌሎች ወደ ትግበራ ሲገቡ አርዓያ የሚሆኑ ልምዶች እንደሚገኝባቸውም ተጠቁሟል።