የሀገር ውስጥ ዜና

የግብርና ዘርፉን ማዘመን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ያግዛል – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

By Melaku Gedif

April 07, 2025

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ዘርፉን ማዘመን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሀገር አቀፍ የግብርና ባለሙያዎች የክህሎት ልማት ሥልጠና መርሐ ግብር ዛሬ በኮምቦልቻ ከተማ ተጀምሯል፡፡

በማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ÷ በሀገር አቀፍ ደረጃ 70 ሺህ የልማት ጣቢያ ሰራተኞች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

በዛሬው ዕለትም 1 ሺህ 300 የሚሆኑ የልማት ጣቢያ ሰራተኞች በይፋ የደረጃ ማሻሻያ ስልጠና መጀመራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የግብርና ዘርፉን ማዘመንና በእውቀት መደገፍ ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ÷ ለግብርና ጣቢያ ሰራተኞች የሚሰጠው ስልጠና ተጠናክሮ እንደሚቀጠል አመልክተዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው ሀገር ትለወጥ ዘንድ በእውቀት የተደገፈ ትውልድ መቅረጽ እንደሚያስፈልግ ገልጸው÷ ግብርናውን ለማዘመን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በከድር መሃመድ