ዓለምአቀፋዊ ዜና

በቴክሳስ ግዛት በኩፍኝ በሽታ የሚያዙ ህሙማን ቁጥር ጨምሯል ተባለ

By ዮሐንስ ደርበው

April 07, 2025

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት በኩፍኝ በሽታ የሚያዙ ህሙማን ቁጥር የመጨመር አዝማሚያ እያሳየ ነው ተባለ።

በበሽታው በምዕራብ ቴክሳስ ግዛት በየካቲት ወር አንድ ታዳጊ ህይወቱን ማጣቱን ያስታወሰው የቢቢሲ ዘገባ፤ አሁን አንድ ተጨማሪ ታዳጊ በኩፍኝ በሽታ ህይወቱን እንዳጣ ገልጿል።

የቴክሳስ የጤና አገልግሎት ዲፓርትመንት መረጃ በየካቲት ወር መጨረሻ ያልተከተበ ልጅ በኩፍኝ በሽታ መሞቱን አስታውሶ፤ በአሜሪካ በአሥር ዓመታት ውስጥ በኩፍኝ በሽታ ሞት ሲያጋጥም የመጀመሪያው ነው ብሏል።

የበሽታውን መከሰት ተከትሎ ተቃውሞ የገጠማቸው የአሜሪካ ጤና ሚኒስትር ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር እሁድ እለት በቴክሳስ ጉብኝት በማድረግ የሟችን ቤተሰብ አጽናንተዋል።

በአካባቢው በአብዛኛ ማህበረሰብ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት አለመከተቡን ገልጸው፤ የኩፍኝ ስርጭትን ለመከላከል በጣም ውጤታማው መንገድ ክትባቱን መውሰድ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በደቡባዊ አሜሪካ ግዛት በዚህ አመት እስከ ከ480 በላይ የኩፍኝ በሽታ ሪፖርት መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፤ በሽታው ወደ አጎራባች ግዛቶች እየተስፋፋ መሆኑ ነው የተነገረው፡፡

በመላው አሜሪካ የፈረንጆቹ 2025 ከገባ ጀምሮ ከ600 በላይ የኩፍኝ ህሙማን የተመዘገበ ሲሆን፤ ይህም የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ባለፈው ከመዘገበው 285 ህሙማን ከእጥፍ በላይ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡