አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢንተርፕራይዞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንተር ፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሴ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ልማትን ለማጠናከር ያለመ የምክክር መድረክ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በተገኙበት በሆሳዕና ከተማ እየተካሔደ ነው።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ኢንተርፕራይዞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል የንግድ ልማት አገልግሎት ድጋፍ እየተደረገ ነው።
አገልግሎቱ ለተመረጡ ከ400 በላይ ለሚሆኑ የማኑፋክቸሪንግ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እየተሰጠ መሆኑን እና በኢኮኖሚ እድገት የሚያበረክቱትን ሚና ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞችን ዉጤታማ ለማድረግ አቅም ግንባታን ጨምሮ በርካታ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዘርፉን ዉጤታማነት የሚያግዝ ፍኖተ ካርታና የፖሊሲ ማዕቀፍ ተግባራዊ መደረጉንም አመልክተዋል፡፡
የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማሻሻል በተሰራው ሥራ 7 ሺህ 525 የአስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሊዝ ፋይናንስ ብድር ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የክልሉ የስራ እድል ፈጠራ እና ኢንተር ፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ በበኩላቸው የአምራች ኢንዱስትሪን ማስፋፋትና ምርታማነት ማሳደግ ላይ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
መንግስት ተኪ ምርትን በሀገር ውስጥ ግብዓት የሚያመርቱና ተጨማሪ እሴት አክሎ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያዎች የሚያቀርቡ ባለሀብቶችን እየደገፈ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በክልሉ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በክልሉ በተለያዩ አምራች ዘርፎች ለተሰማሩ 1 ሺህ 286 አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በመስጠት፤ ምርታማና ተወዳዳሪ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።