Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

መዲናዋን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ፈጠራን የማበረታታትና አምራቾችን የመደገፍ ሥራ እየተሰራ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ፈጠራን የማበረታታትና አምራቾችን የመደገፍ ሥራ እየተከናወነ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ ከተማ አቀፍ የኢትዮጵያ-አዲስ አበባ ታምርት የ2017 ዓ.ም የአምራች ኢንዱስትሪዎች አውደ ርዕይ ዛሬ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ወቅትም የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ቀዳሚ ትኩረት ከተሰጣቸው የኢኮኖሚ መስኮች መካከል አንዱ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

አዲስ አበባ ከተማን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ፈጠራን የማበረታታት፣ አምራቾችን የመደገፍ፣ ፋይናንስ የማቅረብ እና የመስሪያ ቦታዎችን የማመቻቸት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም መሠረተ ልማትን የማሟላት፣ አስፈላጊ ሙያዊ ስልጠናዎችን የመስጠት እንዲሁም ለአምራቾች ድጋፍ የማድረግና ሌሎች በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዘርፉን ከማነቃቃት ባለፈ በተለያዩ ምክንያቶች ማምርት አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት ሥራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን አንስተዋል፡፡

አምራቾች ምርታቸውን ለሸማቹ እንዲያስተዋውቁ፣ የገበያ ትስስር አንዲፈጥሩ፣ ሽያጭ እንዲያከናውኑ እና አምራቾች ከፍ ባለ መድረክ ተገኝተው ልምድ እንዲለዋወጡ የሚያደርግ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች ከ250 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች የተሳተፉበትን አውደ ርዕይ እንዲጎበኙ ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ነዋሪዎች በሀገር ምርት በመጠቀም፣ የሀገር ውስጥ አምራቾችን በመደገፍ እና የሀገር ውስጥ ምርት በመግዛት አምራች እንዱስትሪዎችን እንዲያበረታቱም ጠይቀዋል፡፡

Exit mobile version