አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ሰላምን የመረጡ ታጣቂዎችን ከመቀበል ጎን ለጎን አማራጩን ባልተቀበሉት ላይ እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር ርምጃ ዘላቂ ሰላም እየሰፈነ መምጣቱን የክልሉ ኮሙኒኬሽ ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ ተናገሩ።
በክልሉ እየተገኘ ያለው ሰላም ተቋርጠው የነበሩ የልማት ፕሮጀክቶች ዳግም እንዲጀምሩ እና ህዝቡ በሙሉ አቅሙ በልማት እንዲሳተፍ ዕድል መፍጠሩን ገልጸው፤ አዲስ የተዘረጋው የቀበሌ አደረጃጀት ሰላምና ደህንነትን ከማረጋገጥ አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል።
በበጀት ዓመቱ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ ማህበራዊ ልማት ስራዎችን በማጠናከር፣ በፍትህ እና በገቢ አሰባሰብ ረገድ የተሳካ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
የክልሉ መንግስት ለሰላም የከፈተው በር ትልቅ ውጤት ማምጣቱን ገልጸው፤ ባለፉት ወራት በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሰላም መጥተው የተሃድሶ ስልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
የግጭት አፈታት ሂደቱ በመንግስትና በህዝቡ ተከታታይ ጥረትና ነባሩን የኦሮሞ ገዳ ስርዓት ማዕከል ባደረገ መልክ ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎቹ የተሃድሶ ስልጠና ከወሰዱ በኋላ የስራ እድል እንዲመቻችላቸው እየተደረገ ሲሆን ከፊሎችም በመንግስት መዋቅር ውስጥ እንዲሳተፉ መደረጉን ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹ ወደ ማህብረሰቡ ተቀላቅለው ኑሯቸውን ማሻሻል እንዲችሉና የመንግስትን የልማት ውጥኖች እንዲያግዙ እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።
በክልሉ በአዲስ መልክ በተዘረጉ የቀበሌ መዋቅሮች ህዝቡ ተደራጅቶ ለአካባቢው ሰላምና ደህንነት ዘብ እንዲቆም ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ገልጸዋል።
በተወሰዱ የህግ ማስከበር እርምጃዎችም ሰሜን ሸዋ፣ ምስራቅ ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋ እንዲሁም በምስራቅ እና ምእራብ ወለጋ ዞኖች ሰላም እየተረጋገጠ መምጣቱን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት ለሰላም የከፈተው በር ክፍት መሆኑን አረጋግጠው፤ ህዝቡ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያደርገውን ድጋፍና ጥረት እንዲያጠናክር መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።