Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለመንግሥት ያበደርኩት ብር የለም- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2017 (ኤፍ ም ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመንግሥት ያበደረው ብር አለመኖሩን አስታወቀ፡፡

ባንኩ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባወጣው መግለጫ፤ በዚህ በጀት ዓመትም ሆነ ከዚያ በፊት አንድም ብር ለመንግሥት በቀጥታ አበድሮ እንደማያውቅ በአጽንኦት ገልጿል፡፡

ባንኩ ለመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በግልጽ ካቀረበው እውነታ ባፈነገጠና በተዛባ መልኩ የሪፖርተር ጋዜጣ በዜና አርዕስቱ “መንግስት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደረው አንድ ትሪሊየን ዕዳ እንዳለበት ተገለጸ” በሚል እንዲሁም በሌሎች ጥቂት ሚዲያዎች የመንግስት ዕዳ ብር 1 ነጥብ 3 ትሪሊየን እንደተሻገረና አሁናዊ የመንግስት የብድር ዕዳ ዕድገትን የሚያሳይ በሚመስል መልኩ ተቀናብሮ የቀረበው ዘገባም ሐሰተኛ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የባንኩ መግለጫ ሙሉ ቃል ቀጥሎ ቀርቧል፡-

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮዽያ ንግድ ባንክ ለመንግስት አንድም ብር አበድሮ አያውቅም!

የኢትዮዽያ ንግድ ባንክ በዚህ በጀት ዓመትም ሆነ ከዚያ በፊት አንድም ብር ለመንግስት በቀጥታ አበድሮ አያውቅም። መንግስት ከሀገር ውስጥ የንግድ ባንኮች (በብሔራዊ ባንክ በኩል ለሽያጭ ከሚቀርበው የግምጃ ቤት ሰነድ ግዢ ውጪ) በቀጥታ የመበደር አሰራርም ሆነ ልምድ የለውም። ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ የኢትዮዽያ ንግድ ባንክ በዚህ በተገባደደው ሳምንት ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የስምንት ወራት የስራ አፈጻጸም ማቅረባችንን ተንተርሶ በሪፓርተር ጋዜጣ የዕሁድ ዕትም ቅጽ 30 ቁጥር 2602 መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ታትሞ የተሰራጨው ዜና ከርዕሱ ጀምሮ ለቋሚ ኮሚቴው ከቀረበው ሪፖርትም ሆነ ከእውነታው የተለየና የተዛባ መረጃ ሆኖ አግኝተነዋል። ለምሳሌ በጋዜጣው ዕትም ርዕስ ላይ የተገለጸውና “̋መንግስት ከኢትዮዽያ ንግድ ባንክ የተበደረው አንድ ትሪሊየን ዕዳ እንዳለበት ተገለጸ” የተባለው ዜና ከእውነት የራቀ ከመሆኑም በላይ በሪፖርቱም ፈጽሞ እንደዚህ አይነት ኃሳብ አልቀረበም።

“ባለፉት 15 ዓመታት 92 በመቶ ብድር የተሰጠው ለመንግስት ተቋማት ነው ተብሏል” የሚለው ኃሳብም ስህተት ነው። የቀረበው ሪፖርት በግልጽ እንደሚያሳየው ከለውጡ በፊት የባንካችን የብድር ትኩረት ለመንግስት ተቋማት እንደነበርና ይህ ብድር አድጎ በመጨረሻም ከአምስት ዓመት በፊት እስከ 92% እንደደረሰ እና ከአምስት ዓመት ወዲህ ግን ያ አሰራር የተቀየረና ቅድሚያ ለግል ተበዳሪዎች እየተሰጠ በመሆኑ ፤ ለምሳሌ ያህል በዚህ ስምንት ወራት ከተሰጠው ጠቅላላ ብር 264.65 ቢሊዮን ብድር ውስጥ ከ88% በላይ ብድር የተሰጠው ለግሉ ዘርፍ በመሆኑ አሁን ያለው የመንግስት ተቋማት የብድር ክምችት ድርሻ ወደ 72% ዝቅ ማለቱን ተመላክቷል።

በመሰረቱ ይህ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ዕዳ መንግስት በቀጥታ ራሱ የተበደረው የመንግስት ዕዳ ሳይሆን የተለያዩ እንደ ባንካችን ያሉ የመንግስት የልማት ድርጅቶች የተበደሩት ዕዳ ነው። መንግስት በእነኚህ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ውስጥ የባለቤትነት ድርሻ ቢኖረውም እነዚህ ተቋማት ከአስፈፃሚው መንግስት የተለዩና የራሳቸው ካፒታል ያላቸው፣ እንደ ማንኛውም ድርጅት ንግድ ፍቃድ አውጥተው የሚነግዱ፣ በድርጅታቸው ስም ገንዘብ የሚበደሩ፣ ሊያተርፉም ሆነ ሊከስሩ የሚችሉ፣ ለትርፍ የተቋቋሙ የልማት ድርጅቶች ሲሆኑ ብድሮቹንም የወሰዱት ለራሳቸው ፕሮጀክቶች በመሆኑ ለእነዚህ ተቋማት የተሰጠውን ብድር የመንግስት ብድር ተደርጎ መወሰዱ ስህተት ነው። በሀገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር መሰረት መንግስት ማንኛውም ዓይነት የአጭርም ሆነ የረጅም ግዜ የገንዘብ ፍላጎቱን በሕግ በተቀመጠው አሰራርና ምንጭ ያሟላል እንጂ ከሀገር ውስጥ የንግድ ባንኮች በቀጥታ ብድር የሚወስድበት አግባብ የለም።

ትክክለኛው እውነታ ይህ ሆኖ እያለ አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ዕዳውን መንግስት በቀጥታ የተበደረው ዕዳ እንደሆነ አድርገው በሪፖርተር ጋዜጣም ሆነ ጋዜጣውን ተከትለው በወጡ አንዳንድ የሚዲያ አካላትም መረጃውን በተዛባና በተሳሳተ መልኩ መዘገባቸው ከባንካችን መግለጫ አውድ ውጭ የቀረበ ከመሆኑም በላይ የጋዜጣው ርዕስ በውስጡ ከተጻፉት ኃሳቦች ጋርም ያልተጣጣመ መሆኑ አንባቢያንን ግራ ሊያጋባ እንደሚችል ስለሰጋን እውነታውን ለማሳወቅ ተገደናል።

በጋዜጣው በጉልህ ከተገለጸው በተቃራኒ መንግስት የልማት ድርጅቶች ከባንካችን የተበደሩትንና ለበርካታ ዓመታት ሳይከፍሉ የቆዩትን ከፍተኛ የብድር ገንዘብ በባንካችን ላይ የደቀነውን አደጋ በመገንዘብ የሚከተሉትን እርምጃዎች በመውስድ ባንካችንን ከውድቀት ታድጎታል።

1ኛ. የልማት ድርጅቶቹ ከባንካችን ብድሩን የሚወስዱበት አሰራር አመላለሱን የሚያረጋግጥ ስላልነበረ ይህ አሰራር ሙሉ በሙሉ እንዲቀርና ባንካችን የውሳኔ ነጻነት እንዲኖረው ለመንግስት ተቋማትም ቢሆን አዋጭ የንግድ ኃሳብ ለሚያቀርቡና ባንካችን ስለአመላለሱ እርግጠኛ ለሆነባቸው ብቻ ብድር እንዲሰጥ አቅጣጫ የተቀመጠው ከ5 ዓመት በፊት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ቅድሚያ ለግል ተበዳሪዎች እንዲሰጥ እና የመንግስት የልማት ድርጅቶችም ቀድመው የጀመሩትን ፕሮጀክቶች ሳይጨርሱ ሌላ እንዳይጀምሩ ስለተደረገ ከ5 ዓመት በፊት 92% ደርሶ የነበረው የመንግስት ተቋማት አጠቃላይ የብድር ድርሻ ወደ 72% በአጭር ጊዜ ውስጥ ዝቅ ማለቱ እና የግሉ ተበዳሪዎች ድርሻ ደግሞ ከ8% ወደ 28% በፍጥነት ማደጉ ከፍተኛ ስኬት ሆኖ የቀረበና አንባቢያን ሊያውቁት የሚገባው ጥሬ ሀቅ ነው።

2ኛ. የልማት ድርጅቶቹ በወቅቱ መመለስ ያልቻሉትን ዕዳ በተመለከተ ደግሞ፡-

ሀ. መጀመሪያ የመንግስት ዕዳ እና ኃብት አስተዳዳሪ ድርጅት በማቋቋም እዳዎቹን እንዲከፍል ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። በዚህ ጥረትም ከብር 42.4 ቢሊዮን በላይ እንዲከፈል ተደርጓል።

ለ. ችግሩ በዕዳና ሀብት አስተዳደር ድርጅት ጥረትም ሊፈታ እንደማይችል በመረጋገጡ በዚህ የበጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ አጠቃላይ የአከፋፈል ችግር የገጠመው የመንግስት የልማት ድርጅቶች የብር 845.3 ቢሊዮን ዕዳ ተሰባስቦ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር እንዲዞር እና በየዓመቱ በጀት ተይዞለት እና በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲከፈል ለዚህም ተመጣጣኝ የመንግስት ቦንድ ለባንካችን እንዲሰጥ በፓርላማ ጭምር በማጸደቅ ኃላፊነት የሚሰማውና ቆራጥ መንግስት ብቻ የሚፈጽመው ታሪክ በመስራት ባንካችንን ከውድቀት ኢኮኖሚያችንንም ከትልቅ አደጋ ያዳነ እርምጃ በመውሰዱ መንግስታችንን እጅግ በጣም አመስግነናል፤ አሁንም እጅግ በጣም እናመሰግናለን። ከዚሁ ከተዛወረው ዕዳ ላይ ደግሞ በስምምነቱ መሰረት የመጀመሪያ የግማሽ ዓመት ወለድ በጥር ወር መጀመሪያ ላይ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ብር 38 ቢሊዮን ለባንካችን ተከፍሏል። ስለዚህ መንግስት ባንካችንን ለማዳን ሲል ከልማት ድርጅቶች ተቀብሎ መክፈል ከጀመረው ዕዳ ውጪ የተበደረው ምንም ገንዘብ እንደሌለ ለሕዝባችን ማሳወቅ እንፈልጋለን።

3ኛ. መንግስት ከልማት ድርጅቶች ከተረከበው ከፍተኛ ዕዳ በተጨማሪ ባንካችንን ለማጠናከር የብር 54.7 ቢሊዮን የካፒታል ጭማሪ በማድረግ ከላይ ከተገለጸው የድርጅቶች ዕዳ ጋር ተደምሮ ብር 900 ቢሊዮን የመንግስት ቦንድ እንዲሰጠን በማድረጉም ባንካችንን ሊገጥሙት የሚችሉትን የፋይናንሻል ስጋቶችን መቋቋም ብቻ ሳይሆን ጠንካራ እና ተወዳዳሪ ባንክ እንዲሆን ረድቶታል።

4ኛ. መንግስት ባንካችንን የበለጠ ለማጠናከር ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ላለፉት አምስት ዓመታት ጥልቅ ሪፎርም እንድናደርግ ከፍተኛ ድጋፍ እና አመራር የሰጠን ሲሆን የባንካችን ካፒታል የበለጠ እንዲጠናከርና የውጪ ምንዛሬ ፍላጎታችንን ለማሟላት ያለመ 650 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የካፒታል ማሳደጊያ ድጋፍ እንድናገኝ በማድረጉ ባንካችንን የበለጠ የሚያገዝፈው እና የማይበገር ጠንካራ ተወዳዳሪ የሚያደርገው የመንግስታችን ልዩ ድጋፍ በመሆኑ ባንካችን አሁንም አብዝቶ ያመሰግናል።

እንግዲህ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ በስብሰባው ላይ የቀረቡትና ሕዝባችን ሊያውቃቸው የሚገቡ ብዙ መልካም ዜናዎች እያሉ ያለመታደል ሆኖ አሉታዊ ዜና የመናፈቅ ችግር ጎልቶ በታየበት አኳኋን ሪፖርተርም ሆነ ሌሎች ጥቂት ሚዲያዎች የባንካችንን እጅግ በጣም አንጸባራቂ የስምንት ወራት አፈጻጸም ላይ ጥላሸት ለመቀባት መሞከራቸው አሳዛኝ ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል።

ይልቁንም ሕዝባችን ቢያውቀው የሚጠቅመው ባንካችን በስምንቱ ወራት አፈጻጸም በሁሉም ቁልፍ መለኪያዎች እጅግ በጣም የላቀና ከምንግዜውም እጅግ በጣም ከፍ ያለ ውጤት ማስመዝገቡን ነበር።

ለምሳሌ ያህል፦

  1. በቁጠባ (Deposit)

√ በ8 ወራት ብቻ ብር 367 ቢሊዮን ማሰባሰብ መቻሉ፤ የዚህም ውጤት ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ሲነጻጸር 344% በላይ ዕድገት መሆኑ፣

√ የባንካችን አጠቃላይ ተቀማጭ ብር 1.54 ትሪሊዮን በላይ መድረሱ፤ በዚህም የባንካችን የገበያ ድርሻ የመቀነስ ጉዞውን ቀይሮ በ2.2% በማደግ ወደ 49.3% ከፍ ማለቱ፣

  1. ብድር

√ በ8 ወራት ብቻ ብር 149.2 ቢሊዮን መሰብሰቡ፤ ይህም ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲወዳደር የ66.8% ዕድገት ማስመዝገቡ ፣

√ በዚሁ ጊዜ ውስጥ አዲስ የተለቀቀ ብድር ብር 264.7 ቢሊዮን መሆኑ፤ ይኸውም ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ82.4% ዕድገት ያስመዘገበ መሆኑ፤ ከተለቀቀው አዲስ ብድር ውስጥ ከ88.2% በላይ ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ የተሰጠ መሆኑ፣

√ የባንካችን አጠቃላይ ብድር ከፍተኛ ዕድገት ያስመዘገበ በመሆኑ የባንካችን የብድር የገበያ ድርሻ የመቀነስ አቅጣጫውን ቀይሮ እ.ኤ.አ. ጁን 2024 ከነበረው 42.8% ከፍተኛ ዕድገት በማሳየት 51.7% ከፍ ማለቱ፣

√ የባንካችን የተበላሹ ብድሮች ምጣኔ አምና በተመሳሳይ ጊዜ ከነበረው የ2.7% ወደ 2.3% ዝቅ ማለቱ፤

  1. በውጪ ምንዛሪ

– ባንካችን በ8 ወራት አፈጻጸሙ 2.45 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማሰባሰቡ፤ ይህም ግኝት ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ16.7% እድገት የነበረው መሆኑ፣

– በተለይም ከግል ኃዋላ እና ከሸቀጥ ወጪ ንግድ የተገኘው የውጪ ምንዛሪ እንደቅደም ተከተሉ የ52.2% እና የ58% ከፍተኛ እድገት ማስመዝገብ መቻላቸው፣

– ባንካችን በ8 ወራት ውስጥ አጠቃላይ ለገቢ ንግዱ የከፈለው የውጪ ምንዛሪ መጠን 5.14 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መድረሱ እና ከዚህም ውስጥ ለግሉ ሴክተር የተከፈለው 1.22 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከአምና ተመሳሳይ ወቅቶች ጋር ሲነፃፀር የ58% ከፍተኛ እድገት ማስመዝገቡ መልካም ስኬት ነው፡፡

  1. ካፒታል

የባንካችን አጠቃላይ ካፒታል ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ሲወዳደር የ105% ዕድገት በማሳየት ብር 132 ቢሊዮን መድረሱ፤

  1. አጠቃላይ ሀብት

የባንካችን አጠቃላይ ሀብት በስምንት ወራት በብር 641.7 ቢሊዮን በማደግ ብር 2.07 ትሪሊዮን መድረሱ፤ በዚህ የ44.8% ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገብ በመቻሉ በሀብት የነበረን የገበያ ድርሻ እ.ኤ.አ. በጁን 2024 ከነበረው 43.7% ከፍተኛ ዕድገት በማስመዝገብ 50.4% መድረስ መቻሉ፤

  1. አጠቃላይ ገቢና ወጪ

√ በ8 ወራት ባንካችን በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ የገቢ ዕድገት ያስመዘገበ ሲሆን አጠቃላይ ገቢውም ብር 109 ቢሊዮን መድረሱ፤ ይኸውም ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲወዳደር የ26 % ዕድገት ማስመዝገቡ ፣

√ ባንካችን ጥብቅ የወጪ ቅነሳ ፕሮግራም ሲከተል የነበረና ከፍተኛ የተበላሹ ብድሮች ቅነሳ በማድረጉ ምንም እንኳን በማክሮ ኢኮኖሚው ደረጃ ብዙ ወጪ ጨማሪ ምክንያቶች ቢኖሩም ባንካችን ከመደበኛ የስራ እንቅስቃሴው ያስመዘገበው የወጪ ዕድገት የ2.6 በመቶ ብቻ በመሆኑ አጠቃላይ የመደበኛ ኦፕሬሽን ወጪ ብር 76.7 ቢሊዮን ብቻ መሆኑ፤

  1. መደበኛ ያልተጣራ ትርፍ

√ ባንካችን በ8 ወራት ብር 32.6 ቢሊዮን ያልተጣራ ትርፍ ከመደበኛ ኦፕሬሽን ማግኘት መቻሉ እና ይኸም አፈጻጸም ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ170.5% ዕድገት ያሳየ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት ዓመቱን በሙሉ ተመዝግቦ ከሚያውቀው ትልቁ ትርፍም ከፍተኛ ብልጫ ያሳየ መሆኑ፣

  1. የዲጂታል ግብይት

√ ባንካችን በ8 ወራት በዲጂታል ቻናሎቹ ብቻ ከብር 7.7 ትሪሊዮን በላይ ማንቀሳቀሱ፤ አጠቃላይ የግብይት ብዛትም የ1.27 ቢሊዮን የበለጠ መሆኑ የተንቀሳቀሰው ገንዘብ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ92% ዕድገት ያሳየ ሲሆን የግብይት ብዛት ዕድገትም ከ84% በላይ ዕድገት የነበረው መሆኑ፤

√ ከባንካችን አጠቃላይ የደንበኞች ግብይት በስምንቱ ወራት አማካይ ግብይት 79% በዲጂታል የተስተናገዱ ሲሆን 21%ቱ ብቻ ወደ ቅርንጫፎቻችን ጎራ ብለው የተስተናገዱ መሆኑ ለደንበኞቻችን ምቾት እና ለባንካችን በወጪ ቁጠባም ያገዘና እጅግ በጣም ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገቡ የሚጠቀሱ ከፍተኛ ቁልፍ ስኬቶች ናቸው፡፡

በሌሎች በተቀሩትም ዘርፎች ተመሳሳይ ስኬት የተመዘገበበት በመሆኑ እጅግ በጣም ደስ ይለናል፤ ሁላችሁም የተከበራችሁ የባንካችን ደንበኞችም ሆናችሁ ሀገር ወዳዶች በሙሉ በባንካችን መልካም አፈጻጸም ደስ እንደምትሰኙ እና ከባንካችን ጋር አብሮነታችሁን እንደምታጠናክሩ እናምናለን።

በመጨረሻም ባንካችን ለመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴው በግልጽ ካቀረበው እውነታ ባፈነገጠና በተዛባ መልኩ የሪፖርተር ጋዜጣ በዜና አርዕስቱ “መንግስት ከኢትዮዽያ ንግድ ባንክ የተበደረው አንድ ትሪሊዮን ዕዳ እንዳለበት ተገለጸ” በሚል እንዲሁም በሌሎች ጥቂት ሚዲያዎችም የመንግስት ዕዳ ብር 1.3 ትሪሊዮን እንደተሻገረና አሁናዊ የመንግስት የብድር ዕዳ ዕድገትን የሚያሳይ በሚመስል መልኩ ተቀናብሮ የቀረበው ዘገባ ሀሰተኛ ከመሆኑም ባሻገር ከላይ በዝርዝር በተመላከቱት እውነተኛ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ በባንካችን በኩል የቀረበውን ትክክለኛ ሪፖርት የማያንጸባርቅ እና እነዚህን ለመንግስት የልማት ድርጅቶች የተሰጡትን ብድር ለባንካችን ለመክፈል መንግስት እያደረገ ያለውን ቁርጠኝነት ታሳቢ ያላደረገ በመሆኑ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ሚዲያዎች የተላለፈው የተዛባና የተሳሳተ ዘገባ እንዲታረም እናሳስባለን።

Exit mobile version