Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በድሬዳዋ ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የችግኞች ዝግጅት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተዘጋጁ መሆናቸው ተገልጿል።

በከተማ አስተዳደሩ የአካባቢ፣ የደን ልማት እና አየር ንብረት ባለስልጣን የደን ልማት ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ይመር÷ በዘንድሮ ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለተከላ እየተዘጋጁ ካሉ ችግኞች መካከል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ የፍራፍሬ ችግኞች እንደሚገኙበትም ጠቁመዋል፡፡

ችግኝ ተክሎ ማሳደግ ለድሬዳዋ የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት አቶ ማስረሻ፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከተተከሉት ችግኞች 72 በመቶ መፅደቃቸውን ተናግረዋል።

ይህም የጎርፍ አደጋን በመከላከል እና የገጠሩን ማህበረሰብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ መሠረታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ችግኞቹ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ በተጨማሪ ለደን፣ ለጥላ እና ለከተማ ውበት የሚያገለግሉና በመጠናቀቅ ላይ ለሚገኘው የኮሪደር ልማት ማስዋቢያነት ጭምር የሚውሉ እንደሆኑ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version