የሀገር ውስጥ ዜና

ሌ/ጄ ታደሰ ወረደ ትግራይ ውስጥ ያለውን ክፍተት ሞልተው ወደ ፊት ሊወስዱ ይችላሉ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Adimasu Aragawu

April 08, 2025

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ አሁን ትግራይ ውስጥ ያለውን ክፍተት ሞልተው ወደ ፊት ሊወስዱ ይችላሉ የሚል እምነት በብዙ አካላት የታመነ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፕሬዚዳንትነት የስልጣን ርክክብ ሥነ-ሥርዓት በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ባለፈው አንድ ወር ገደማ የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት፣ የፕሪቶርያን ስምምነትና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡን ምክር በማከል ሰፊ ውይይቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

የአቶ ጌታቸው ረዳ የሥልጣን ዘመን በሕጉ መሠረት ሲያበቃ የሚቀሩ ቁልፍ ሥራዎችን ለማከናወን ጊዜያዊ መንግሥቱ መቀጠለ አለበት የሚል ድምዳሜ በመያዝ ሽግግሩን ማን መርቶ ከግብ ሊያደርስ ይችላል የሚሉ ውይይቶች ሲደረጉ መቆየታቸውንም አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ በዛሬው ዕለት በሰላማዊ መንገድ በአዲስ ባህል የሥልጣን ሽግግሩንና ቅብብሎሹን ለማካሄድ የተዘጋጀ ፕሮግራም በይፋ አከናውነናል ብለዋል።

ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ ባለፉት ሁለት ዓመታት የአቶ ጌታቸው ረዳ ምክትል ሆነው ሲያገለግሉ በመቆየታቸው የነበሩ ድካሞችንና ጥንካሬዎችን በግልጽ እንደሚገነዘቡም በመልዕክታቸው ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ምክንያት አሁን ትግራይ ውስጥ ያለውን ክፍተት ሞልተው ወደ ፊት ሊወስዱ ይችላሉ የሚል እምነት በብዙ አካላት የታመነ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ የትግራይ ሕዝብ የጠማውን ሰላምና ልማት እንደ ሌሎች ወንድሞቹ ወጥቶ የመግባት መሻት በማሳካት ለኢትዮጵያም ለአፍሪካም እጅግ ጠቃሚ ነገር ሠርቶ ለማለፍ ታሪክ የሰጣቸውን ዕድል እንደሚጠቀሙበት ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡