አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ጋዜጠኞችን ወይም የሚዲያ ባለሙያዎችን የመመዝገብም ሆነ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ የመስጠት ተግባርም ሆነ ኃላፊነት እንደሌለው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አስገነዘበ፡፡
ባለስልጣኑ ባወጣው መግለጫ፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ለጋዜጠኞች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ለመስጠት እና የጋዜጠኞች ምዝገባ ለማከናወን ውይይት እና እንቅስቃሴ መጀመሩን ደርሸበታለሁ ብሏል፡፡
ይህን ተከትሎም የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት፣ ጋዜጠኞች እና የሙያ ማኅበራት ጉዳዩን በተመለከተ የሕጋዊነት ጥያቄ እና ስጋቶቻቸውን እያቀረቡልኝ ነው ሲል ገልጿል፡፡
በመሆኑም የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤቱ ጋዜጠኞችን ወይም የሚዲያ ባለሙያዎችን የመመዝገብም ሆነ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ የመስጠት ተግባርና ኃላፊነት በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 እንዳልተሰጠው ባለስልጣኑ አሳውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንም ለዚህ ተግባር ዕውቅና የማይሰጥ መሆኑን ነው በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ ያሳወቀው፡፡