ቢዝነስ

የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሂደት እንዲሳካ እየተሰራ ነው – ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)

By abel neway

April 08, 2025

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሂደት በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲሳካ እየተሰራ ነው ሲሉ የዓለም ንግድ ድርጅት ብሔራዊ የድርድር ኮሚቴ ዋና ተደራዳሪ የሆኑት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የዓለም ንግድ ድርጅት ብሔራዊ የድርድር ኮሚቴ ከአባል ሀገራት ጋር በሚደረጉ የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነቶች እንዲሁም የ6ኛው የዓለም ንግድ ድርጅት የሥራ ቡድን ስብሰባ የዝግጅት ሥራዎች የሚመክር ስብሰባ በዛሬው ዕለት አካሂዷል።

በመጪው ሐምሌ ወር የሚካሄደው 6ኛው የዓለም ንግድ ድርጅት የስራ ቡድን ስብሰባ በከፍተኛ ትኩረትና በበቂ ዝግጅት ለማካሄድ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር)፤ የድርድር ሂደቱን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማሳካት በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።

በ2026 ካሜሮን በሚካሄደው የዓለም ንግድ ድርጅት የሥራ ቡድን ስብሰባ የኢትዮጵያ የአባልነት ሂደት ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ ስለመሆኑ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

በቅርቡ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት 5ኛው የሥራ ቡድን ስብሰባ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ቆይታ የነበረው የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ልዑካን ቡድን የተሳካ ሥራ ማከናወኑ ይታወሳል።