Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በቀጣዮቹ ጊዜያት የትግራይን ህዝብ ልማት እና የለውጥ ፍላጎት የሚያሳኩ ተግባራት ይከናወናሉ- ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀጣዮቹ ጊዜያት የትግራይን ህዝብ ልማት እና የለውጥ ፍላጎት የሚያሳኩ ተግባራት እንደሚከናወኑ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ ገለጹ።

የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር የርዕሰ መስተዳድር ርክክብ ሥነ ስርዓት በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።

በዚህም ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ፥ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድርነትን ተረክበው የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር የተልዕኮ አፈጻጸም የቃል ኪዳን ሰነድን ፈርመዋል።

በሥነ-ስርዓቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ሌተናል ጄኔራል ታደሰ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያልተሰሩ በቀጣይ መሰራት ያለባቸው በርካታ ተግባራት አሉ።

ከፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸም ጋር የተያያዘ ብቻም ሳይሆን የተፈጠሩ የጸጥታ፣የፖለቲካ እንዲሁም የኢኮኖሚ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ ችግሮች ቀላል አለመሆናቸውን ገልጸው፥ በዚህ ላይ ለውጥ ለማምጣት በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

በቀጣዮቹ ጊዜያት የትግራይን ህዝብ የልማት ጥያቄ እና የለውጥ ፍላጎት የሚያሳኩ ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።

እንዲሁም የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር እንደሚሰራ እንዲሁም ያሉ ውጥረቶችን የማርገብ ስራ እንደሚከናወን አመልክተዋል።

የህዝቡን የለውጥ ፍላጎት ለማሳካት የሚሰራበት መሆኑን ነው ያነሱት።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፥ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ስራዎችን መስራቱን ገልጸዋል።

ለአብነትም አገልግሎቶችን የመመለስ፣ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲሁም ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራ መሰራቱን ገልጸው፤ ነገር ግን በቂ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

የፌዴራል መንግስት ለተጨማሪ አንድ ዓመት የጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዲቀጥል ማድረጉ አዎንታዊ ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል።

የትግራይን የሰላም እና የለውጥ ፍላጎት ለማሳካት እና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በውስጥ የነበሩ የፖለቲካ ንትርኮች የፕሪቶሪያ ስምምነት በተሟላ መልኩ እንዳይከናወን በማድረግ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

እርስ በእርስ በመጓተት መቀጠል እንደማይቻል የገለጹት አቶ ጌታቸው፥ የተገኘውን ሰላም ለማደብዘዝ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን በመገንዘብ ሰላሙን ለማጽናት ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አሁን ላይ በትግራይ ህዝብ ዘንድ ያለው የሰላም እና የለውጥ ፍላጎት ሊቀለበስ የማይችል መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህን ከግምት በማስገባት የቀሩ ስራዎችን ማጠናቀቅ ስራ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ነው ያመላከቱት።

Exit mobile version